ኢትዮጵያ ከድህነት ቅነሳና ከስርዓተ ምግብ ለውጥ አንጻር ያደረገችው ስኬታማ ጉዞ ከፍተኛ ዕውቅና ሊቸረው የሚገባ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለድህነት ቅነሳ በሰጠው ልዩ ትኩረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ህይወት በላቀ ደረጃ ማሻሻል መቻሉ ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የማሕበራዊ ልማት ጉባዔ በኳታር ተካሂዷል።
በኳታር ዶሃ በተካሄደው በሁለተኛው ዓለም አቀፍ የማሕበራዊ ልማት ጉባዔ ድህነትን ለመቀነስ እና ሌሎች የማሕበራዊ ልማት ግቦችን እንዲሁም የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር፣ ኢ-ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና ንግድ ስርዓት ማሸሻል እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ተሰጥቶታል።
ጉባዔው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተዘጋጀ ሲሆን የማሕበራዊ ልማት ምሰሶዎች በሆኑት ድህነት ቅነሳ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ማሕበራዊ አካታችነት ላይ በማተኮር ተካሄዷል።
ቁጥራቸው ከ14 ሺህ የሚልቁ ከመንግሥታት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከመንግሥት ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከአካዳሚክ ተቋማት እና ሌሎች በርካታ አካላት የተውጣጡ ተሳታፊዎችም የታደሙበት ነበር።
በኳታር ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፋይሰል አልይ፤ በጉባኤው በህንድ እንዲሁም ፋኦ አዘጋጅነት በተመቻቹ የጎንዮሽ ወይይቶች ላይ በመገኘት ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳ ዘመቻዎች ላይ ያላትን ልምድ አካፍለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ያሉት አምባሳደር ፋይሰል፤ ከብሔራዊ በጀቷ ውስጥ ወደ አራት በመቶ የሚጠጋው ለግብርና እና ለገጠር ልማት የተመደበ ነው ሲሉ አብራርተዋል። ይህንኑ የድህነት ቅነሳን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡
በጉባኤው ላይ በተደረጉ የጎንዮሽ ስብሰባዎች የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፤ 70 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ ለመርኃ ግብሩ ቃል ተገብቷል። ይህ ድጋፍ ከእውቅና ባለፈ በቀጣይነት ለመርሃ ግብሩ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ተብሏል።
አምባሳደር ፌይሰል የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምን በቴክኒክ እና በገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡትን ሁሉንም አጋሮች ከልብ አመስግነው፤ በማህበራዊ ልማት ዙሪያ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የልማት አጋሮቿ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል በቅርቡ ኢትዮጵያ ያስተናገደችው የተ.መ.ድ የስርዓተ ምግብ ጉባዔ ጋር በተገናኘ በተዘጋጀው የጎንዮሽ መድረክ ላይ አምባሳደር ፈይሰል ከስርዓተ ምግብ ለውጥ አንጻር የኢትዮጵያን ስኬታማ ጉዞ አቀርበዋል።
የተ.መ.ድ ምክትል ዋና ጸኃፊ አሚና ሞሃመድ በመድረኩ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ለውጥ ማምጣቷን እና የተ.መ.ድ የስርዓተ ምግብ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷን በመጠቀስ እውቅና ሰጥተዋል።
በሁለተኛው ዓለም አቀፍ የማሕበራዊ ልማት ጉባዔ ድህነትን ለመቀነስ እና ሌሎች የማሕበራዊ ልማት ግቦችን እንዲሁም የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር፣ ኢፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና ንግድ ስርዓት ማሸሻል እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #UN #socialdevelopment #summit