Search

በሀረር ውበት እና ታሪካዊ ቅርሶች ተደንቀናል - የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች

ዓርብ ኅዳር 19, 2018 177

የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ከሚገኘው የተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ላይዘን ቢሮ ጋር በመተባበር በአዘጋጁት ፕሮግራም የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ አባላት ዛሬ በሀረር ከተማ ጉብኝት አድርገዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበችውን የጁገል ግንብን እና የሀረር የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ጎብኝተው፤ በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረው የኢኮ ቱሪዝም ፓርክ የጅብ መመገብ ትዕይንት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ላይዘን ኦፊስ ዋና ዳይሬክተር ሪታ ቢሱናት (ዶ/ር)፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች በጎበኟቸው የልማትና የቱሪዝም ሃብቶች መደነቃቸውን ተናግረዋል።
ሀረር በውስጧ የያዘቻቸው ውብና ታሪካዊ ቅርሶች ይበልጥ ሊጎበኙ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
 
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፣ በሀረሪ ክልል የቱሪዝም መስህቦችን መልሶ በማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ጉብኝቱ በዋናነት በክልሉ ያሉትን የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ የውጭ ቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
 
በጉብኝቱ ከ40 በላይ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።