Search

አዲስ አበባ፡ ከሰው ተኮር ልማት እስከ ዘመናዊ መዲና ግንባታ

ዓርብ ሚያዝያ 23, 2018 74

የትላንቱ ትውስታና የታሪክ ሽግግር

የአሁኗን አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረችው ከተማ ጋር ማነጻጸር፣ በአንድ ትውልድ ዘመን ውስጥ ሊታሰብ የማይችልን የታሪክ ሽግግር እንደመመልከት ይቆጠራል። ትላንት በአእምሯችን የታተመው የከተማዋ ምስል የተቆራረጠ የከተማ ዕቅድ፣ በቆሻሻ የተሞሉ የወንዝ ዳርቻዎች ለእግረኛ የማይመቹ መንገዶችና የድህነት መገለጫ የሆኑ የተጎሳቆሉ መንደሮች ስብስብ ነበረች።

ከተማዋ ለዘመናት በቆየ የልማት ቸልተኝነትና ውጤታማ ባልሆነ የከተማ አስተዳደር ምክንያት፣ ነዋሪዎቿ ለከፋ ማኅበራዊ ቀውስና ለተመሰቃቀለ ኑሮ ተጋልጠው ቆይተዋል።

ይህ የከተማነት ዝቅታና የዜጎች ክብር አለመጠበቅ አዲስ አበባን የአፍሪካ መዲናነቷን የሚመጥን ግርማ እንዳይኖራት አድርጓት ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። ዛሬ ግን ድቅድቅ ትዝታ ተገፎ ከተማዋ ሰውን ማዕከል ባደረገ ጥልቅ የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች።

የፖሊሲ ሽግግርና የበጀት ቁርጠኝነት

የአዲስ አበባ የለውጥ ጉዞ ስኬት ምስጢር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የበጀትና የፖሊሲ ማዕቀፍ መከተሉ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ከበጀቱ ውስጥ 70 በመቶ በላይ ለልማት ፕሮጀክቶች በመመደብ፣ የከተማዋን  ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎቿን ሕይወት የሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ አተኩሯል።

በፍጥነት እያደገ ከመጣው በጀቷ ጋር ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የምትመድበውን ከፍተኛ በጀት እያሳደገች መቀጠሏ ከተማዋ ለልማት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል። ይህ የፋይናንስ አቅም ከተማዋን የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግብ (SDG 11) ተምሳሌት በማድረግ፣ አካታች፣ ደኅንነቷ የተጠበቀና ጠንካራ ከተማ የመገንባት ራዕይን እያሳካ ይገኛል።

ማኅበራዊ ፍትህ እና ትውልድን የማነጽ ተልዕኮ

በትውልድ ግንባታው ሂደት ከተማ አስተዳደሩ የወሰደው ርምጃ ማኅበራዊ ፍትህን በተግባር ያረጋገጠ ነው። በ264 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው የምገባ ፕሮግራም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ፣ የትምህርት ማቋረጥን በከፍተኛ ደረጃ ቀንስዋል። ይህም አዲስ አበባ እንደ ዓለም አቀፉ "ሚላን የከተማ ምግብ ፖሊሲ ስምምነት" (Milan Urban Food Policy Pact) ዕውቅና እና ሽልማቶችን አሸናፊ አድርጓታል።

ከዚህ በተጨማሪ ለሀገር ውለታ የዋሉ አረጋውያንና አቅመ ደካማ ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ በከተማዋ የተገነቡት 30 "የተስፋ ብርሃን" የምገባ ማዕከላት 35 ሺህ በላይ ዜጎችን በየቀኑ በመመገብ የከተማዋን የሰብዓዊነት አሻራ አድምቀውታል። የከተማ ነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለል በየሳምንቱ የሚካሄዱ የሰንበት ገበያዎችና አዳዲስ የገበያ ማዕከላት አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነቱን በመከላከል ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ነው።

የዜጎች ክብርና የሰብዓዊነት አሻራ

የከተማዋ ለውጥ ሌላኛው ምሰሶ የዜጎችን ክብር ማደስ ነው። "ለነገዋ" የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ከአስከፊ የጎዳና ላይ ኑሮ በማውጣት በ18 የሙያ መስኮች አሰልጥኖ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ አድርጓል። የሠልጣኞቹ የ97.5 በመቶ የብቃት ማረጋገጫ (COC) ውጤት የሥልጠናውን ጥራት የሚያሳይ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የአቅመ ደካሞች ቤቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መታደሳቸው፣ ከተማዋ ለማንኛውም ዜጋ የምትመችና የዜጎችን ክብር የምታስጠብቅ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ስኬት ነው።

የኮሪደር ልማትና የዲጂታል አስተዳደር ሽግግር

አዲስ አበባን ወደስማርት ከተማ’ (Smart City) የቀየረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ የከተማዋን የመሠረተ ልማት ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አድርጎታል። የኮሪደር ልማቱ ሰፊ የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት መስመሮችን፣ ፓርኮችንና ዘመናዊ የፍሳሽና የቴሌኮም አውታሮችን በማካተት የከተማዋን ገጽታ ቀይሯል። ይህ ልማት ከተማዋን ለነዋሪዎች "ሊኖርባት የሚገባ መዲና" (Livable Metropolis) ከማድረጉም በላይ፣ ለበርካታ ወጣቶችና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የወንዝ ዳርቻ ልማቶችም ተበክለው የነበሩ ስፍራዎችን ወደ አረንጓዴ መዝናኛነት በመቀየር የአየር ጥራቱንና የከተማዋን ውበት አሻሽለዋል።

ይህንን ዘመናዊነት ለማጠናከር አስተዳደሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት እየተጠቀመ ይገኛል። የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን ከማስፋፋት ጀምሮ ስማርት ፖሊስ’ (Smart Police) ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት በዘመናዊ መንገድ መምራት ተችሏል። በተጨማሪም የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን (One-stop services) በማስፋፋት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ነዋሪውን ያማከለ ማድረግ ተችሏል።

የአፍሪካ የሕክምናና የዲፕሎማሲ ማዕከል

አዲስ አበባን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል (Health Tourism Hub) ለማድረግ የተያዘው ግብ በተጨባጭ ውጤቶች እየታገዘ ይገኛል። ግዙፍና ዘመናዊ ሆስፒታሎች ግንባታና የነባር ጤና ተቋማት ማስፋፊያ፣ ኢትዮጵያውያን ለሕክምና ወደ ውጭ የሚሄዱበትን የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ አዲስ አበባን የአፍሪካውያን የጤና መዳረሻ እያደረጋት ነው። እነዚህ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና የቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ በማድረግ፣ የአፍሪካ መዲናነቷንና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ወደ ተሻለ ከፍታ አሸጋግረውታል።

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያካሄደ ያለው የለውጥ ጉዞ፣ ዜጎችን ከድህነት የመታደግ ሥራን ከከተማዋ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ የቱሪዝም እና የዘመናዊ መሠረተ ልማት እድገት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው። የህዝብን ኑሮ መሰረት ያደረገው ይህ የልማት አቅጣጫ፣ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ተስማሚ፣ ብሎም በአፍሪካ አህጉር ግንባር ቀደም ስማርት ከተማ እንድትሆን መንገድ የጠረገ መሆኑን አሁን ላይ እየታዩ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶች ይመሰክራሉ።

በለሚ ታደሰ