Search

ሉክሰምበርግ፦ ነዋሪዎቿንም ሆኑ ጎብኚዎቿን በነፃ በማጓጓዝ በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር

ዓርብ ሚያዝያ 16, 2018 235

ሉክሰምበርግ በቆዳ ስፋቷም ሆነ በሕዝብ ብዛቷ አነስተኛ ብትሆንም፣ በወሰደችው ደፋርና አርቆ አሳቢ እርምጃ የዓለምን ቀልብ መሳብ ችላለች። በቤልጂየም፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ የምትዋሰነው ይህች ወደብ አልባ ሀገር፣ እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 2020 ጀምሮ ለመላው ዜጎቿም ሆነ ለሀገሪቱ ጎብኚዎች "ነፃ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት" በመስጠት በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፋለች። ይህ እርምጃ ሀገሪቱ ለዜጎቿ የምትሰጠውን ክብር እና ለአካባቢ ጥበቃ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳየችበት ትልቅ ማሳያ ሆኗል።

በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ መሠረት፣ ሉክሰምበርግ በነፍስ ወከፍ ገቢ ከዓለም ባለጸጋ ሀገራት ተርታ የምትመደብ ሲሆን፣ ይህ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅምና የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንደ ነፃ ትራንስፖርት ያለ ግዙፍና በጀት የሚጠይቅ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ትልቅ የጀርባ አጥንት ሆኖላታል። ሀገሪቱ እንዲህ ያለውን ውሳኔ እንድትወስን ካስገደዷት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ በሀገሪቱ የሚታየው ከፍተኛ የመኪና ቁጥር ነው። በየ1,000 ነዋሪዎች 647 የግል መኪኖች ያሉ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ከፍተኛው የመኪና ባለቤትነት መጠን ነው። ይህ ሁኔታ ያስከተለውን የትራፊክ መጨናነቅ፣ የድምፅና የአየር ብክለት ለመቀነስ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2020 "ዘላቂ የመንቀሳቀስ ስትራቴጂ" ነድፎ ወደ ተግባር ገብቷል።

የዕቅዱ ዋነኛ ግብ ዜጎች የግል መኪናቸውን ትተው ይበልጥ ለአካባቢ ተስማሚና ቀልጣፋ የሆኑ የሕዝብ ትራንስፖርቶችን እንዲጠቀሙ ማበረታታት ሲሆን፣ አገልግሎቱ ከተጀመረባቸው ያለፉት አምስት ዓመታት ውስጥም አስገራሚ ስኬቶች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ የባቡር ተጠቃሚዎች ቁጥር በ2019 ከነበረበት 25 ሚሊዮን በ2024 ወደ 31.3 ሚሊዮን አድጓል። በተመሳሳይ በ2019 የነበረው 6.2 ሚሊዮን የትራም አገልግሎት ተጠቃሚ በ2024 ወደ 31.7 ሚሊዮን በመመንጠቅ የአምስት እጥፍ እድገት አሳይቷል። ይህ ስኬት የመጣው አገልግሎቱ ነፃ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት በመሠረተ ልማትና በአዳዲስ ዘመናዊ ትራሞች ላይ ባደረገው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ጭምር ነው።

 

ምንም እንኳን አገልግሎቱ ለተጓዦች ነፃ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን ለሥራ ማስኬጃው ከፍተኛ ወጪ ያወጣል። እ.ኤ.አ. በ2020 ለዘርፉ የወጣው 590 ሚሊዮን ዩሮ በ2025 ወደ 1.1 ቢሊዮን ዩሮ ከፍ እንዲል የተደረገ ሲሆን፣ መንግሥት ቀደም ሲል ከቲኬት ሽያጭ ይገኝ የነበረውን 41 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ትቶ አጠቃላይ ወጪውን በታክስ ገቢ ለመሸፈን ወስኗል። የሀገሪቱ የትራንስፖርትና የሕዝብ ሥራዎች ሚኒስትር ዩሪኮ ባከስ እንደገለጹት፣ ነፃ ትራንስፖርት ከምልክትነት ባለፈ የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት የሚያሻሽል ተጨባጭ እርምጃ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።

ሀገሪቱ ባገኘችው ስኬት ሳትወሰን እስከ 2040 የሚዘልቅ አዲስ ብሔራዊ ዕቅድ ይፋ አድርጋለች። በዚህም በሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ፈጣን የዋይ-ፋይ (Wi-Fi) አገልግሎት ማሟላት፣ የጉዞ መረጃዎችን በቅጽበት ለተጓዦች የሚያደርስ ዲጂታል ሥርዓት መዘርጋት እና የትራም መስመሮችን እስከ ሀገሪቱ ዳርቻዎች ድረስ ማስፋፋት ዋነኛ ግቦቿ ናቸው። የሉክሰምበርግ ተሞክሮ ለዓለም የሚያስተምረው ትልቅ ቁምነገር፣ የአየር ብክለትንና መጨናነቅን ለመቀነስ ነፃ አገልግሎትን ከጥራት፣ ከተደራሽነትና ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር ማቀናጀት ያለውን ፋይዳ ነው። ሉክሰምበርግ የወደፊቱ ዓለም ከተሞች ምን መምሰል እንዳለባቸው እያሳየች ያለች የዘመናዊው ዓለም የትራንስፖርት ተምሳሌት ሆናለች።

 

በላሉ ኢታላ