በቻይና ሃይናን ግዛት የሚገኘው የቻንጂያንግ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ "ዩኒት 4" ግንባታ እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የቻይና ናሽናል ኑክሌር ኮርፖሬሽን (CNNC) አስታውቋል።
ለ60 ወራት እንዲቆይ ታቅዶ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ በፈረንጆቹ 2027 መጀመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ወር በተከናወነ ስኬታማ ተግባር፣ 52 ሜትር ዲያሜትር፣ 12 ሜትር ቁመት እና 415 ቶን ክብደት ያለው የውጪ ብረት ጉልላት በሪአክተሩ ላይ ተገጥሟል።
ይህንን ግዙፍ አካል አንስቶ ለመግጠም ሁለት ሰዓታት ብቻ የፈጀ ሲሆን፣ ለሥራውም 4 ሺህ ቶን የማንሳት አቅም ያለው ግዙፍ ክሬን ጥቅም ላይ ውሏል።
ይህ ጉልላት የ"ሁዋሎንግ ዋን" ሪአክተር የድርብ ጥበቃ ሥርዓት አካል በመሆን፣ ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች እንዳይወጡ የመከላከል ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ለጣቢያው ዩኒት 3 እና 4 ግንባታ በአጠቃላይ 40 ቢሊዮን ዩዋን ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ሁለቱም ዩኒቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።
ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር በዓመት 18 ቢሊዮን ኪሎዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከመደገፉም በላይ፣ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን በ11.68 ሚሊዮን ቶን በመቀነስ ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ይህ ስኬት ቻይና በንጹህ ኢነርጂ ዘርፍ የጀመረችውን ጉዞ ይበልጥ የሚያፋጥንና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ብቃቷን የሚያሳይ ሆኖ ተመዝግቧል።
በቢታኒያ ሲሳይ