Search

የዲጂታል አብዮት መሪዋ ኢትዮጵያ - የአፍሪካን የቴክኖሎጂ ነፃነት ፍለጋ

ሓሙስ ሚያዝያ 15, 2018 78

ዓለማችን በቴክኖሎጂ ምህዋር በፍጥነት እየተሽከረከረች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ የዲጂታል ልዕልና የብልጽግና፣ የሉዓላዊነት እና የዕድገት መለኪያ ሆኗል።

በዚህ የለውጥ ማዕበል ውስጥ አፍሪካን ከዳር ተመልካችነት ወደ መሪ ተዋናይነት ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት፣ ኢትዮጵያ የፈነጠቀችው የዲጂታል ብርሃን አህጉራዊ ዕውቅናን አግኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው፣ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላስመዘገበችው አኩሪ ስኬት የተሰጠ ትልቅ የክብር አክሊል ነው።

ይህ ሹመት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ አዲሲቷ የተስፋ ዓድማስ የሆነችው ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2010 ወዲህ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" መሠረት በማድረግ ለሠራችው የላቀ ስትራቴጂካዊ ሥራ የተሰጠ ፍትሐዊ ምላሽ ነው።

የአፍሪካ ኅብረት በሹመት ደብዳቤው ላይ እንዳሰፈረው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ለውጤታማነት እና ለአሳታፊ ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማስቻል ረገድ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

ይህ አባባል ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ነፃነትን እና አቅምን በመገንባት የአፍሪካ የዲጂታል ፋና ወጊ መሆኗን በጉልህ የሚያረጋግጥ ነው።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የኢትዮጵያ አዲስ የአቅም ማማ

የሰው ሠራሽ አስተውሎት የነገዋን ዓለም የሚቀርጽ ግዙፍ አቅም መሆኑን ቀድማ የተረዳችው ኢትዮጵያ፣ ዘርፉን በሀገር ደረጃ ለማሳደግ ታሪካዊ እርምጃዎችን ወስዳለች።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የዚህ የለውጥ ጉዞ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ተቋሙ በግብርና፣ በጤና፣ በፋይናንስ፣ በትራንስፖርት እና በመረጃ ደኅንነት ዘርፎች የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማፍለቅ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከኢንስቲትዩት ምሥረታ አልፋ፣ ዘርፉን በፖሊሲ ለመምራት "ሀገራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ" ነድፋ ወደ ትግበራ ገብታለች።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፍትሐዊ፣ ኃላፊነት የተሞላበት እና የዜጎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖ እንዲያገለግል የሚያስችለው ይህ ስትራቴጂ፣ ለአፍሪካ ሀገራትም እንደ ሞዴል የሚያገለግል ነው።

ከዚህም ባሻገር፣ ራሱን የቻለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የተያዘው ዕቅድ፤ ምርምርን፣ የክህሎት ልማትን እና አህጉራዊ ትብብርን ይበልጥ በማጠናከር የነገውን ትውልድ ለዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር የሚያዘጋጅ ነው።

የዲጂታል ጤና (Digital Health) - ቴክኖሎጂ ለዜጎች ሕይወት 

የጤናው ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት በቀጥታ የሚነካ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን ሰፊ ሪፎርም አድርጋለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዲጂታል ጤና አህጉራዊ መሪ ሆነው መሾማቸው፣ ኢትዮጵያ የሕክምና መረጃ ሥርዓቶችን በማዘመን፣ የኤሌክትሮኒክ የሕክምና መዝገቦችን (EMR) ወደ ተግባር በመቀየር እና ቴሌ-ሜዲሲንን (Tele-medicine) በማስፋፋት ላመጣችው ለውጥ የተሰጠ ዕውቅና ነው።

በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት ከወረቀት አሠራር ተላቀው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሳሰሩበት ሥርዓት በመገንባት ላይ ይገኛል።

ይህ መሆኑ ታካሚዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭት ስርዓቱ ግልጽነት እንዲኖረው፣ እንዲሁም የጤና መረጃዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዘው ለፖሊሲ ውሳኔና ለበሽታ ቅድመ-ትንበያ እንዲያገለግሉ አስችሏል።

የለውጡ መሠረት፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025

እነዚህ አህጉር አቀፍ ስኬቶች በአየር ላይ የተንጠለጠሉ ሳይሆኑ፣ ጽኑ በሆነው "የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ ላይ የተገነቡ ናቸው። ባለፉት ስምንት ዓመታት መንግሥት የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል።

የቴሌኮም ዘርፉን ሊበራላይዝ በማድረግ የውድድር መንፈስን መፍጠሩ፣ "ቴሌ ብር" እና መሰል የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ፣ እንዲሁም ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ትግበራ መጀመሩ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽኑ ቁልፍ ማሳያዎች ናቸው።

የኢ-መንግሥት (e-government) አገልግሎቶች መስፋፋት ዜጎች ከመንግሥት የሚያገኙትን አገልግሎት ስሉጥ፣ ቀልጣፋና ከሙስና የጸዳ እንዲሆን አድርጎታል።

በፈጠራ ሥነ-ምህዳሩ (Innovation Ecosystem) ላይ የተደረገው ኢንቨስትመንትም ወጣቶች የሥራ ፈጣሪነት አቅማቸውን እንዲያወጡና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የነገ ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ ሰፊ ዕድል ከፍቷል።

የአፍሪካን ሉዓላዊነት በቴክኖሎጂ ማረጋገጥ

የአፍሪካ ኅብረት በሹመት ደብዳቤው ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት "ለአፍሪካ ሉዓላዊነት" ያለውን ፋይዳ ማንሣቱ እጅግ ጥልቅ ትርጉም አለው።

21ኛው ክፍለ ዘመን እውነተኛ ነፃነትና ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው የራስን መረጃ በራስ የመቆጣጠር፣ ቴክኖሎጂን የማመንጨት እና ከዓለም አቀፍ የዲጂታል ጥገኝነት በመላቀቅ ነው።

ኢትዮጵያ በተግባር እያሳየች ያለው ይህንኑ ነው። ኢትዮጵያዊያን መሐንዲሶች በገዛ ሀገራቸው ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሲያበለጽጉ፣ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ነፃነት እየተረጋገጠ መሆኑን ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የአፍሪካ ኅብረት ኃላፊነት ሲረከቡ፣ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ወደ አህጉሪቱ ለማስፋፋት፣ የአፍሪካ ሀገራት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ፉክክር ውስጥ አፍሪካ የራሷን ጠንካራ ድምፅ ይዛ እንድትወጣ ለማስቻል ታሪካዊ አደራ ተቀብለዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና የአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሹመት፤ ኢትዮጵያ በለውጥ ዓመታት የተከለችው የቴክኖሎጂ ችግኝ አፍርቶ፣ አህጉርን ለማጠለል መብቃቱን የሚያሳይ ደማቅ የድል ብስራት ነው።

ከማኅበራዊ ሚዲያ ፍጆታ ባለፈ ቴክኖሎጂን ለምግብ ሉዓላዊነት፣ ለጤና ዋስትና፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለመረጃ ደኅንነት ማዋል እንደሚቻል ኢትዮጵያ በተግባር አሳይታለች።

ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና አጣምሮ የያዘው ይህ የለውጥ ጉዞ፣ ሀገራችንን ዐዲሲቷ የተስፋ ዓድማስ፣ የአፍሪካን ደግሞ የዲጂታል ትንሣኤ ባለቤት እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም።

የጀመርነው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ የልዕልና ማማ የሚያወጣት፣ ትውልድ የሚሻገር ታላቅ ታሪካዊ ቅርስ ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ