የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲሱ አራዳ ፓርክ ምረቃ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፕሮጀክቱ ዋነኛ መነሻ እና ማጠንጠኛ ሰው መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ፒያሳና አካባቢው ለነዋሪዎች የማይመች፣ ንጽህናው ያልተጠበቀና አስከፊ ድህነት የሚታይበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር ቅድሚያ በመስጠት፣ በደባልነት እና በቆጥ ላይ ጭምር ተጠጋግተው ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ለኑሮ ምቹ በሆኑ አካባቢዎች እንዲኖሩ መደረጉን ከንቲባ አዳነች ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱ እነዚህ ነዋሪዎችን አካትቶ ሁሉንም ተነሺዎች ለኑሮ ወደ ሚያስደስትና ለልጆች አስተዳደግ ወደሚመች ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ማዛወሩንም ተናግረዋል።
ይህ የልማት ሥራ ማኅበረሰቡን ከብክለትና ከበሽታ በመታደግ፣ የኢትዮጵያውያንን ክብር በሚመጥን መልኩ የተሠራ መሆኑንም ከንቲባዋ አብራርተዋል።
በአካባቢው የነበረው አስከፊ ድህነትም ዛሬ ላይ ተቀርፎ ስፍራው ወደ ቀድሞ ታሪካዊ ስሙ "አራዳ" መመለሱን በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል።