Search

ኢትዮጵያን ያስቀደመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰው ሠራሽ አስተውሎት ራዕይ

ሓሙስ ሚያዝያ 15, 2018 93

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያሳየች ያለችው ፈጣን ሽግግር በአፍሪካ አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን እየሳበ ይገኛል።

የዚህ ታላቅ ለውጥ ግንባር ቀደም መሃንዲስ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) እንደ ቅንጦት ሳይሆን የሀገርን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን መሠረታዊ መሣሪያ አድርገውታል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት በሚያደርጓቸው ንግግሮች የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዕድገት ኢትዮጵያን እንደማያሰጋት ይልቁንም ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላት በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

በተለይም "እኔን የሚያሰጋኝ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዕድገት ሳይሆን የእኛ መተኛት ነው" በማለት ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ለመጠቀም ፈጣን ዝግጅትና ንቁ ተሳትፎ እንደሚሻ በተደጋጋሚ ያሳስባሉ።

"ዘግይቶ የመድረስ ዕድል" (Latecomer Advantage) እና የተቋማት ግንባታ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቴክኖሎጂ ፍልስፍና ዋና ማጠንጠኛ አንዱ "ዘግይቶ የመድረስ ዕድል" የሚለው ፅንሰ-ሐሳብ ነው።

ኢትዮጵያ በቀደሙት የኢንዱስትሪ አብዮቶች ውስጥ በንቃት ባለመሳተፏ የደረሰባትን ወደኋላ መቅረት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካኝነት ሌሎች ሀገራት ያለፉባቸውን ረጅም እና አድካሚ ደረጃዎች በመዝለል (Leapfrogging) ወደ ዘመናዊው የዲጂታል ምዕራፍ በቀጥታ መሸጋገር ትችላለች የሚል እምነት አላቸው። 

ይህንን ዕሳቤ ወደ ተግባር ለመለወጥም 2012 . የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት እንዲመሠረት ያደረጉ ሲሆን፣ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እና ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማቅረብ እየሠራ ይገኛል።

በተጨማሪም በዓለም ላይ በዓይነቱ ሁለተኛ የሆነውን እና ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥናት ብቻ የተሰየመ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁ የዚህ ራዕይ አካል ነው።

የቴክኖሎጂው ተግባራዊ አጠቃቀም በልዩ ልዩ ዘርፎች

በጤናው ዘርፍ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዙ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት የጡት ካንሰርን፣ የስኳር በሽታን እና የልብ በሽታን አስቀድሞ መለየት የሚያስችሉ ሲስተሞችን አበልጽጓል።

ከዚህም ባለፈ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች መረጃ መስጠት የሚችለው "መላ" የተሰኘው ሥርዓት፣ በጤና ተቋማት ውስጥ ያለውን የመረጃ ልውውጥ እና የምርመራ ሂደት ያቀላጥፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋነኛ ገቢ ምንጭ የሆነውን የቡና ምርት ከበሽታ ለመታደግ ሰው ሠራሽ አስተውሎት መፍትሔ ሆኖ መጥቷል።

"ደቦ ቡና" የተሰኘው መተግበሪያ አርሶ አደሮች የቡና ቅጠልን ፎቶ በማንሳት ብቻ ተክሉ የደረሰበትን በሽታ እንዲለዩ እና የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያስችላቸዋል።

በፋይናንስ ዘርፍም ቢሆን የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ያለ መያዣ ብድር የሚሰጥበት "ሚቹ" የተሰኘው መድረክ ለግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ አነስተኛ ነጋዴዎች 50 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ ተጠቃሚነትን አረጋግጧል።

አህጉራዊ አመራር እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕይታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላቸው ቁርጠኝነት እና ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን እያገኘ መጥቷል።

በዚሁ በሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው በአፍሪካ ኅብረት ጉበኤ መሾማቸው ለዘርፉ የሰጡት አመራር እና ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ለምታከናውነው የላቀ ሚና የተሰጠ ትልቅ እውቅና ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አመራር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ ሉዓላዊነት እና ለተሳታፊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማስቻል ረገድ ትልቅ እገዛ እያደረገ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት የዲጂታል መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ የኢ-መንግሥት አገልግሎቶችን በመተግበር፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም እና ሀገራዊ ስትራቴጂ በመንደፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ፋና እንድትሆን አድርጓታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ በቴክሎጂው ረገድ ልትከተለው የሚገባውን አቅጣጫ አስመልክተው ሲናገሩ "አፍሪካ በግልጽ ስትራቴጂካዊ ራእይ እና ደፋር ኢንቨስትመንቶች፣ በሥነ-ምግባር መርሆች፣ አካታችነት እና ዘላቂነት ላይ ተመሥርታ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማትን በራሷ መንገድ መምራት አለባት" ይላሉ። 

ይህም አፍሪካ የራሷን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ቴክኖሎጂ አፍላቂ መሆን እንዳለባት ያሳያል። 

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ መዳረሻ ለማድረግ በሚያልመው ጉዞ ውስጥ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ ዋነኛ ሞተር እየታየ ሲሆን ይህም የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያሳልጠው ይጠበቃል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #Ethiopia #PMAbiyAhmed #Africa #AI