Search

የሁለት ወንዞች ታሪክ እና ዕጣ ፈንታቸውን የጻፉ ባለራዕዮች - ከቴምስ እስከ አዲስ

ሓሙስ ሚያዝያ 22, 2018 66

ታሪክ የሚመዘገበው በወረቀት ላይ ብቻ አይደለም። ታሪክ አንዳንዴ በውኃ ላይ ይፈስሳል። የአንድ ሕዝብ ሥልጣኔ፣ የከተማነት ደረጃ እና የመሪዎቹ ራዕይ የሚለካው ከተማዋን ለሁለት ከፍለው በሚፈስሱ ወንዞቿ እንክብካቤ ነው።

ዛሬ በሁለት የተለያዩ አህጉራት፣ በሁለት የተለያዩ ዘመናት ግን ደግሞ በአንድ ዓይነት የውድቀት እና የትንሣኤ ታሪክ ውስጥ የሚያልፉ ሁለት ታላላቅ ወንዞችን እንመለከታለን። የለንደኑ ቴምስ እና ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚዘልቀውን የአዲስ አበባ ወንዝ።

ሁለቱም ወንዞች የነዋሪዎቻቸውን ትኩረት የተነፈጉ፣ የቆሻሻ መጣያ እና የብክለት ምሳሌ የነበሩ፤ ነገር ግን ውድቀትን እንደ ዕጣ ፈንታ ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑ በላራዕይ መሪዎቻቸው የገዘፉ ሐሳቦች የለውጥ ምሳሌ መሆን የቻሉ ሆነዋል።

አራዳን ሰንጥቆ በሚያልፈው የአዲስ አበባ ወንዝ ላይ የተሠራው እና ዛሬ የተመረቀው የአራዳ ፓርክ፣ የአንድ ትልቅ ፕሮጀክት ማሳያ ብቻ አይደለም፤ የአዲስ አበባን በመሠረታዊነት የመለወጥ፣ የወንዞቿን ዕንባ የማበስ እና የከተማዋን ክብር የመመለስ የታሪክ ዐሻራ እንጂ።

መለያዋ ከመሆኑ አስቀድሞ የእንግሊዝ ‘ነውር’ የነበረው ቴምስ ወንዝ

19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ለንደን የዓለም የንግድ እና የፖለቲካ ማዕከል ነበረች። ነገር ግን በመሐሏ የሚፈስሰው የቴምስ ወንዝ የከተማዋ ትልቁነውር’ ነበር። በወቅቱ ለንደን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች ነገር ግን የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቷ ከጥንት የሮማውያን ዘመን ያልዘለለ ነበር። የፋብሪካ ኬሚካሎች፣ የሰው እና የእንስሳት ቆሻሻዎች በሙሉ በቀጥታ ወደ ቴምስ ይፈስሱ ነበር።

በዚህ ምክንያትም በ1858 . ለንደን "ታላቁ ግማት" (The Great Stink) ተብሎ የሚጠራው አስከፊ ክስተት ገጠማት። በዚያ በጋ ወቅት ከፍተኛ ሙቀት በመከሰቱ የወንዙ ውኃ ቀነሰ፣ ቆሻሻው ግን አልቀነሰም። ከወንዙ የሚወጣው መጥፎ ሽታ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ በወንዙ ዳርቻ የሚገኘው የእንግሊዝ ፓርላማ ስብሰባውን ለማካሄድ አልቻለም። መስኮቶችን በፀረ-ተባይ በታጠቡ ጨርቆች ለመሸፈን ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።

የለንደን ነዋሪዎች ወንዙን እንደ "የሞት ሸለቆ" ይመለከቱት ነበር። ኮሌራ እና ሌሎች በሽታዎች በከተማዋ ተንሰራፉ። በወቅቱ ብዙዎች "ወንዙን ማዳን አንችልም" በሚል ተስፋም ቆርጠው ነበር። ሆኖም ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ዲስራኤሊ እና ድንቅ መሐንዲሱ ሰር ጆሴፍ ባዛልጌት ይህንን ውርደት ወደ ድል ለመቀየር ወሰኑ።

ባዛልጌት በዘመኑ "የማይቻል" ተብሎ የሚታሰበውን ግዙፍ የከርሰ ምድር የፍሳሽ ቱቦ መስመር ዘረጋ። ቆሻሻው ከወንዙ ተለይቶ ወደ ማከሚያ እንዲሄድ ተደረገ። ዛሬ ቴምስ የለንደን የቱሪዝም ዋልታ፣ የባለ ቅኔዎቿ የሐሳብ ምንጭ፣ የከተማዋ ፖስት ካርድ እና የአውሮፓ ንፁህ ወንዝ ለመሆን በቅቷል።

የአዲስ አበባ ስውር ቁስል

አዲስ አበባ ስሟን ያገኘችው ከውኃዎቿ ነው። ሆኖም፣ ስሟ እየገዘፈ በሄደ ቁጥር፣ ለስሟ መገኘት ምክንያት የሆኑት ወንዞቿ ግን እየረከሱ እና እየጠፉ መጡ።

ባለፉት 130 ዓመታት ከተማዋ እያደገች ስትሄድ ወንዟን የረሳችው ትመስል ነበር። አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ መድረክ "የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና" እየተባለች ስትሞገስ፣ በመሐሏ የሚያልፉት ወንዞቿ ግን የሽንት እና የቆሻሻ መጣያ ሆነው ቆይተዋል። የወንዞች ዳርቻ የወንጀለኞች መሸሸጊያ በዙሪያቸው ሚኖሩ ዜጎችም ለጎርፍ፣ ለሽታ እና ለሌች ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ተጋልጠው ኖረዋል።

የአዲስ አበባ ወንዞች ከየትኛውም ልማቱ የተገለሉ ነበሩ። ሕንፃዎች ፊታቸውን ወደ አስፋልት፣ ጀርባቸውን ደግሞ ወደ ወንዙ አዙረው ነበር። ይህ ደግሞ ወንዙን የከተማዋ "የጓሮ ቆሻሻ መጣያ" እንዲሆን አድርጎታል። ልክ እንደ ቴምስ፣ አራዳን አቋርጦ የሚያልፈው የአዲስ አበባው ወንዝም የከተማዋስውር ውርደት’ ሆኖ ለበርካታ ዐሥርተ ዓመታት ዘልቋል።

ወንዙ ውበት መሆኑ ቀርቶ የከተማዋ ስውር ቁስል ሆነ። በዳርቻው የሚኖሩ ዜጎች በየክረምቱ በጎርፍ ስጋት ይጨነቃሉ፤ በየበጋው ደግሞ በአስከፊ ሽታ ይታወካሉ። ከዚህም ባለፈ፣ ወንዙ ቁጥጥር የሚደረግበት መተላለፊያ ባለመኖሩ ለወንጀለኞች መደበቂያ፣ ለከተማዋ ደኅንነት ደግሞ ስጋት ሆኖ ቆይቷል። በአንድ ወቅት ለአዲስ አበባ መወለድ ምክንያት የሆነው ወንዝ፣ በጊዜ ሂደት ከተማዋ ልትደብቀው የምትፈልገው ትልቅ ‘ነውር’ ሆኖ ኖረ።

የታሪክ ለውጥ እና የኮሪደር ልማት ራዕይ

አንድ ከተማ እንዲለወጥ የግድ መሐንዲስ ብቻ ሳይሆን ባለራዕይ መሪ ያስፈልገዋል። በለንደን ዲስራኤሊ እንደነበረው ሁሉ፣ በአዲስ አበባም የወንዞችን ጥቅም የተረዳ እና ከተማዋን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ የቆረጠ አመራር መጣ።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሲታሰብ ብዙዎች "የማይቻል ነው” በሚል ተጠራጥረውት ነበር። ነገር ግን የፕሮጀክቱ ዋና ግብ ከተማዋን ለነዋረዎቿ  ምቹ ማድረግ ነው።

ከእንጦጦ እስከ ቃሊቲ የሚዘልቀው የወንዝ ዳርቻ ልማት የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት አካቷል፦

ልክ እንደ ለንደኑ ባዛልጌት ሥራ፣ የቤቶች እና የሕንፃዎች ቆሻሻ በቀጥታ ወደ ወንዙ እንዳይገባ የሚከላከሉ ግዙፍ የፍሳሽ ቱቦዎች በወንዙ ዳርቻ ተቀብረዋል።

የወንዙ ዳርቻዎች በድንጋይ ንጣፍ ተገንብተዋል፤ አረንጓዴ ተክሎች ተተክለዋል፤ የወንዙ ፍሰት እንዲስተካከል ተደርጓል። ወንዙ ለብቻው እንዲፈስስ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡ ሊጠቀምበት የሚችልባቸው ፓርኮች፣ የእግረኛ መንገዶች እና የብስክሌት መስመሮች ተገንብተዋል።

የአራዳ ፓርክ - የዛሬው እና የነገው ድምቀት

ዛሬ የተመረቀው የአራዳ ፓርክ የዚህ ታላቅ ራዕይ ማሳያ ነው። ይህ ስፍራ በአንድ ወቅት በቆሻሻ የተሞላ እና ማንም ሊጠጋው የማይፈልገው የወንዝ ዳርቻ ነበር።

ዛሬ ግን ስፍራው ተቀይሯል። የቆሸሸው ውኃ በንፁህ ፏፏቴዎች፣ በድንቅ የአርክቴክቸር ሥራዎች እና በለመለመ ሳር ተተክቷል።

ይህ ፓርክ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን ይዞ መጥቷል። በከተማዋ መሐል ተጨናንቆ ለሚውል ነዋሪ የወንዝ ድምፅ እየሰማ የሚዝናናበት ቦታ ሆኗል፤ በፓርኩ ዙሪያ ያሉ የንግድ ተቋማት እሴታቸው ይጨምራል። ቱሪስቶችም አዲስ አበባን በውበትም እንዲያስታውሷት ማድረግ ጀምሯል። አዲስ አበባ አሁን ፊቷን ወደ ወንዞቿ መልሳለች። ከአሁን በኋላ "የአፍሪካ መዲና" ስንል በኩራት የምናሳየው ንፁህ ወንዝም ይኖረናል።

የወንዞች ትንሣኤ - የሀገር ትንሣኤ

የቴምስ ወንዝ መታደስ ለንደንን የዓለም የንግድ ማዕከል እንድትሆን መንገድ ጠርጓል። የአዲስ አበባ ወንዞች መታደስም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ  ማሳያ ነው።

ታሪክ ባለራዕዮችን የሚያስታውሰው በገነቡት ሕንፃ ብቻ ሳይሆን፣ ባነጹት የሕዝብ ስብዕናባስወገዱት ቆሻሻ እና በፈጠሩት ውበትም ነው።

ዛሬ የአራዳ ፓርክ ሲመረቅ፣ እኛ የምናከብረው የአንድን ፓርክ መጠናቀቅ ብቻ አይደለም፤ የአዲስ አበባን አዲስ ማንነት ነው። በአንድ ወቅት የፍሳሽ ማስወገጃ እና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ተብሎ የተፈረደበት የአዲስ አበባው ወንዝ፣ ዛሬ ከሞት ተነሥቷል።

ትናንት እንዳላይህ ተብሎ ጀርባ የተሰጠው ወንዝ፣ ዛሬ የከተማዋ የፊት ገጽ ሆኗል። ይህ ወንዝ አሁን ቆሻሻን ሳይሆን ተስፋን ያፈስሳል፤ መጥፎ ሽታን ሳይሆን የሰላም ትንፋሽን ይለግሳል።

የለንደኑ ቴምስ የፈጀውን የረጅም ጊዜ ለውጥ አዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለማድረግ መቻሏ፣ የራዕዩን ግዝፈት እና የትጋቱን ጥልቀት ያሳያል። አዲስ አበባ አሁን ስሟን መስላለችበእውነትም "አዲስ አበባ" ሆናለች።

የአራዳ ፓርክ መከፈት፣ አዲስ አበባ የድሮ ቁስሏን ሽራ፣ አዲስ አበባነቷን አድሳ ለዓለም የምታሳይበት የድል አደባባይ ነው። ታሪክ ነገን ሲመዘግብ እንዲህ ይላል፦ከተማዋ ፊቷን ወደ ውኃዎቿ መለሰች፤ ውኃዎቿም ውበቷን መለሱላት።

በነቢዩ ወንድወሰን