Search

ሩዋንዳ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ግዥ 30 በመቶው የኤሌክትሪክ እንዲሆን ወሰነች

ዓርብ ሚያዝያ 16, 2018 72

የሩዋንዳ መንግሥት በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የአየር ብክለትን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት የመንግሥት ተቋማት ከሚገዟቸው አዳዲስ ተሽከርካሪዎች መካከል 30 በመቶው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ወሰነ።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 14 ቀን 2026 በሀገሪቱ በመሠረተ ልማት ሚኒስቴር የወጣውና ሰሞኑን ይፋ የሆነው ይኸው መመሪያ፣ በሩዋንዳ የሚገኙ ሁሉም የመንግሥት በጀት አስተዳዳሪዎች በግዥ ዕቅዳቸው ውስጥ ይህንን መስፈርት እንዲያካትቱ ያስገድዳል።
የሩዋንዳ የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዣን ደ ዲዩ ኡዊሀንጋንዬ እንደገለጹት፣ ውሳኔው ከተፈረመበት ዕለት ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን ዋነኛ ዓላማውም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ ረገድ የሀገሪቱን ጥረት ማገዝ ነው።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ተጠቃሚነት ለማስፋፋትም የሩዋንዳ መንግሥት ቀደም ሲል የተለያዩ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ አድርጓል።
ከእነዚህም መካከል ለተሽከርካሪ መሙያ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ታሪፍ መወሰን እንዲሁም ለተሽከርካሪዎቹና ለመለዋወጫዎቻቸው ከቀረጥ ነፃ የመግባት መብት መስጠት ይገኙበታል።
ሀገራችን ኢትዮጵያም በተመሳሳይ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ረገድ ሰፊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የምትገኝ ሲሆን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚነትም በአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት አንዷ ሆናለች።
መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ የቀረጥ ማሻሻያ ከማድረጉም ባለፈ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች በስፋት እንዲገነቡ እና በሀገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥሙ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በተለይም በነዳጅ ግዥ ላይ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ትልቅ ፋይዳ ያለው ይህ የሽግግር ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረትም ሀገራችን እስከ እ.ኤ.አ 2030 ድረስ 500 ሺህየኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገራችን መንገዶች ላይ ለማሰማራት ግብ አስቀምጣ እየሠራች ትገኛለች።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ