Search

ጋቦን ከ16 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ጥብቅ ሕግ አወጣች

ሰኞ ሚያዝያ 05, 2018 52

ጋቦን ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አካውንት እንዳይከፍቱ የሚከለክል ጥብቅ ሕግ አውጥታለች።
ይህም ሀገሪቱን አዳጊዎችን ከዲጂታል ዓለም አደጋዎች ለመጠበቅ እንዲህ ዓይነት ሕግ በማውጣት በአፍሪካ ቀዳሚዋ ያደርጋታል።
የጋቦን ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን (HAC) ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ሕጉ በዋናነት አዳጊዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ከሚሰነዘሩ ጥቃቶች፣ ከሐሰተኛ መረጃዎች እና ከማይመጥኑ ይዘቶች ለመከላከል ያለመ ነው።
በአዲሱ ሕግ መሠረት፣ አዳጊዎች ለትምህርታዊ ዓላማ ካልሆነ በቀር በማንኛውም ማህበራዊ ሚዲያም ሆነ የኢንተርኔት መድረኮች ላይ አካውንት እንዳይከፍቱ በሕግ ይከለከላል።
ይህ አዲስ መመሪያ ሕጉን በማያስከብሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ልጆቻቸውን በአግባቡ በማይቆጣጠሩ ወላጆች ላይ ጥብቅ ተጠያቂነትን ያስከትላል።
የጋቦን መንግሥት የወሰደው ይህ እርምጃ እንደ ፌስቡክ እና ቲክቶክ ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጠንካራ የዕድሜ ማረጋገጫ ዘዴዎችን እንዲተገብሩና ሕገ-ወጥ አካውንቶችን በፍጥነት እንዲዘጉ የሚያስገድድ ነው።
የሕጉን ተፈጻሚነት የሚከታተለው የጋቦን ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን፤ የዲጂታል መድረኮቹ ለሚቀርቡባቸው ማንኛውም ቅሬታዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ የመስጠት እና በ72 ሰዓታት ውስጥ ደግሞ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ እንደተጣለባቸው አርቲ ዘግቧል።
ይህ የጋቦን ውሳኔ አዳጊዎች የዲጂታል መድረኮችን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለውን እንቅስቃሴ የሚከተል ነው።
አውስትራሊያ በ2024 ተመሳሳይ ሕግ ያፀደቀች ሲሆን፣ በ2025 መጨረሻ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አድርጋለች። ፈረንሳይ እና ዴንማርክም የዕድሜ ገደቡን ወደ 15 ዓመት ከፍ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ