በቻይና የመኖሪያ ቤቶች እና የኢንዱስትሪ ሕንጻዎች የሚገነቡበት መንገድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አዲስ መልክ እየያዘ ይገኛል።
ሀገሪቱ የሞዱላር (3D) ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቤቶችን ክፍሎች በፋብሪካ አምርቶ የመገጣጠም ዘዴን በስፋት እየተገበረች ሲሆን፣ ይህም የግንባታውን አቅምና ፍጥነት በእጅጉ ጨምሮታል።
ይህ ስልት ግንባታን ከተለመደው አድካሚ አሠራር ወደ ዘመናዊ የፋብሪካ ምርት በመቀየር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፣ ለኢንዱስትሪውም አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
በዚህ ዘመናዊ አሠራር ደንበኞች የሚፈልጓቸውን የቤት ዓይነቶች፣ ዋጋ እና ዲዛይን ባሉበት ሆነው በኢንተርኔት መምረጥ ይችላሉ።
ደንበኛው ምርጫውን ካሳወቀ በኋላ ቤቶቹን የሚሠራው ድርጅት በፍጥነት ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ ከግንባታው ሥራ 90 በመቶ የሚሆነው ክፍል በፋብሪካ ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተመርቶ ደንበኛው በፈለገው ቦታ ላይ እንዲገጣጠም ይደረጋል።
ይህ አሠራር የግንባታ ጊዜን በ75 በመቶ፣ የካርቦን ልቀትን በ30 በመቶ፣ እንዲሁም የአቧራና የድምፅ ብክለትን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ የቤቱ ክፍል የራሱ መለያ መታወቂያ ስላለው ለጥገና እና ክትትል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ቴክኖሎጂው በቻይና ከተሞች ብቻ ሳይወሰን በገጠር መንደሮችም ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው።
ከዚህም ባለፈ የመኖሪያ ቤቶችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እና ትላልቅ ፋብሪካዎችን ለመገንባት የሚወስደውን ጊዜ በማሳጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ቻይና ይህን ዘመናዊ አሠራር ወደ አረንጓዴ ግንባታ ለምታደርገው ጉዞ እንደ ትልቅ ሞተር እየተጠቀመችበት ሲሆን፣ የቴክኖሎጂው ከጊዜ ወደ ጊዜ መዳበር እና የመንግሥት ድጋፍ የግንባታ ዘርፉን ወደ አዲስ የዕድገት ደረጃ አሸጋግሮታል።
ከቻይና ውጪ ያሉ ሀገራትም የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። ለምሳሌ ጃፓን ለመሬት መንቀጥቀጥ የማይበገሩ ቤቶችን በፍጥነት ለመሥራት ቴክኖሎጂውን በስፋት ትጠቀምበታለች።
ሲንጋፖር በመንግሥት በሚገነቡ ቤቶች ላይ የሰው ኃይል እጥረትን ለመቅረፍ የሞዱላር ዘዴን ግዴታ ስታደርግ፣ እንደ ስዊድን ባሉ ሀገራት ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቤቶች በፋብሪካ ተመርተው የሚገጣጠሙ ናቸው።
ይህም ቴክኖሎጂው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለከተሞች ዕድገት እና ለዘላቂ ልማት ዋነኛ መፍትሄ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል።
ኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት እና የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት የሞዱላር ግንባታን እንደ አማራጭ መጠቀም ጀምራለች።
በአሁኑ ወቅት በመንግሥት እና በግል ዘርፉ በርካታ ግንባታዎች በዚህ ስልት እየተሠሩ ሲሆን፣ ሂደቱም እጅግ አዋጭ መሆኑ ታምኖበታል።
ይህም ሀገራችን በግንባታው ዘርፍ ለምታደርገው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለከተሞች ውበት ትልቅ ተስፋን የሰነቀ ጅማሮ ሆኖ ተመዝግቧል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#EBC #China #ModularConstruction #GreenTechnology #Innovation #Ethiopia