ተቋማት በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ መሆን እና የሀገርን ስም ማስጠራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
12ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ትናንትና በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሲካሄድ፣ የጥራት ሽልማት አሸናፊ መሆን ለተቋማት የልህቀት ጉዞ መጀመሪያ እንጂ መዳረሻ አለመሆኑን ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።
ተሸላሚዎች ሽልማቱን እንደ ትልቅ መነሻ በመጠቀም ጥራትን የዕለት ተዕለት መገለጫ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ጥራት በአጋጣሚ የሚከሰት ሳይሆን በጥልቅ በማሰብ፣ በመሥራት እና በልፋት የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
ተቋማት ጥራትን በቋሚነት ማስጠበቅ፣ የሰው ኃይል ብቃትና እውቀትን ማሳደግ እንዲሁም የአመራርና ሠራተኛን ትጋት መጨመር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የጥራት ሽልማት መርሐ ግብሩ ተቋማትን ለተሻለ ሥራ የሚያተጋ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ተቋማት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጎልቶ በመውጣት የሕዝብን ይሁንታ ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ