Search

በቢሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከረሀብ የታደጉት የአረንጓዴው አብዮት አባት - ዶ/ር ኖርማን ቦርላግ

እሑድ ኅዳር 21, 2018 426

ኖርማን ኤርነስት ቦርላግ የተወለዱት .. በመጋቢት 25 ቀን 1914 በዩናይትድ ስቴትስ አዮዋ ግዛት በሚገኝ አንድ ትንሽ የገጠር መንደር ውስጥ ነበር።

የልጅነትና የወጣትነት ጊዜያቸውን በትውልድ መንደራቸው ቤተሰቦቻቸውን በእርሻ ሥራ ላይ በማገዝ  አሳልፈዋል። ይህም  በኋለኛው ሕይወታቸው ውስጥ የአፈርን ዋጋ፣ የአርሶ አደሩን ድካም እና የሚያጋጥመውን ተግዳሮት እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።

ኖርማን ቦርላግ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ካጠናቀቁ በኋላ፤ 1933 ወደ ሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የባችለር ዲግሪያቸውን በደን ልማት ወስደዋል። ከዛም በኋላ ትምህርታቸውን በመቀጠል 1942 Plant Pathology የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል።

ከዚያም በሮክፌለር ፋውንዴሽን እና በሜክሲኮ መንግሥት ትብብር የተቋቋመው የምርምር ፕሮግራም አካል ውስጥ ተካተው ወደ ሜክሲኮ ተጓዙ።

የዚህ ተልዕኮ ዓላማም በወቅቱ የምግብ አጥረት ችግር ውስጥ የነበረችውን  ሜክሲኮ የስንዴ ምርቷን ማሳደግ የሚችል ምርምር ማካሄድ ላይ ያተኮረ ነበር።

በዚህ ቆይታቸውም ለሜክሲኮ የስንዴ ምርት መቀነስ ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ለይተው አወቁ። ከነዚህ ዋንኛ ችግሮች መካከል አንደኛው የስንዴ ዝገት ወይም (Stem Rust) የሚባለው ችግር ነው።
ይህ በፈንገስ የሚመጣ የአዝርዕት በሽታ፣ የስንዴ ምርቱን ሙሉ በሙሉ የሚበላ አውዳሚ በሽታ ሲሆን ለምርት እጥረት መከሰት ዋንኛው ምክንያት ነበር።

ሌላው ችግር ደግሞ  የሰብል መውደቅ ችግር ነው። አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ተጠቅመው ምርት ለማግኘት ሲሞክሩ የሰብሉ ግንድ እና የዘሩ ብዛት ቢጨምርም ግንዱ የዘሩን ክብደት መሸከም ስለማይችል መሬት ላይ ይወድቅና ምርቱ ይበላሽ ነበር።

ዶክተር ኖርማን ቦርላግ የችግሩን መፍትሔ በሚገባ ካጠኑ በኋላ፤ እነኚህን ችግሮች የሚያስወግድ፣ በሽታን የሚቋቋም፣ ጠንካራ ግንድ ያለው በፍጥነት የሚያድግ የስንዴ ዘር ለማግኘት ምርምራቸውን ቀጠሉ።

በዚህ ምርምራቸውም የስንዴ ሰብሎችን የሚበላውን ፈንገስ የመከላከልና የመቋቋም አቅም ያለው ዘር ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ ከታይዋን ካስመጧቸው  የስንዴ ዝርያዎች ጋር በማዋሀድ  አጭር ግንድ ያለው ስንዴ (Dwarf Wheat) የሚባለውን ምርጥ ዘር ማግኘት ቻሉ።

ይህ በዶክተር ቦርላግ የተፈጠረው የተሻሻለ ዝርያ በሽታን የመከላከል አቅም ያለው፣ ብዙ ምርት መስጠት የሚችል እና ጠንካራ ግንድ ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ፤ በተለያዩ የአየር ሁኔታዎች ውስጥ በዓመት ሁለቴ መመረት የሚችል ነበር።

ከዶ/ ቦርላግ ምርምር በፊት የሜክሲኮ ገበሬዎች በዓመት አንዴ ብቻ የሚያመርቱ ሲሆን፤ የአየር ንብረትንና በሽታዎችን  መቋቋም የሚችለው ስንዴ ዝርያ በብዛት ተመርቶ ለአርሶ አደሮች በመሰራጨቱ ሜክሲኮ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስንዴ ምርት ራሷን ወደመቻል ተሸጋገረች።

ዶክተር ኖርማን ቦርላግ ይህ የሜክሲኮ ተልዕኳቸውን በአመርቂ ውጤት ካሳኩ በኋላ፤ ትኩረታቸውን ወደ ደቡብ ኤዥያ ሀገራት አደረጉ።

ይህ ወቅት በተለይ 1960ዎቹ አጋማሽ በተለይም ሕንድና ፓኪስታን በከባድ ድርቅና የምርት መቀነስ ችግር ውስጥ ገብተው፤ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ብዛት መመገብ የሚችል የስንዴ ምርት ማምረት ያልቻሉበትና በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ የተጋረጠበት ወቅት ነበር

ይህን የተገነዘቡት ዶክተር ኖርማን ቦርላግ፥ ሁለቱ ሀገራት የተጋረጠባቸውን ረሀብ ለማስወገድ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን የምርጥ ዘር ለመላክ ወሰኑ።

ሆኖም ፖለቲከኞች የተሻሻለውን ዘር ለመቀበል ማቅማማት ጀመሩ። ይህን የተረዱት ቦርላግ  የፖለቲከኞቹን ውሳኔ ወደጎን በማለት ያመረቱትን የስንዴ ዘር ወደ እነዚህ አገሮች እንዲላክ በጽናት ተሟግተው  በሕንድ ካሉ ምሁራን ጋር በመተባበር ራሳቸው ወደ ሕንድ ተጉዘው ምርጥ ዘሮቹ እንዲሞከሩና በፍጥነት እንዲስፋፉ አደረጉ። በፓኪስታንም ይህንኑ እንዲተገበር አደረጉ።

በሕንድ እና ፓኪስታን በሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት ላይ አዲሱ የዶክተር ኖርማን ቦርላግ ግኝት በሆነው ዘር እንዲሸፈን ተደረገ።

ይህ ወቅት በሕንድና ፓኪስታን የአረንጓዴው አብዮት ፍንዳታ እውን የሆነበት ወቅት ነበር፤ በአዲሱ ዘር የተሸፈኑት መሬቶች በአስገራሚ ሁኔታ በሰብል ተሸፈኑ። በፓኪስታን የስንዴ ምርት 5 ዓመታት ውስጥ ብቻ ከእጥፍ በላይ ጨመረ።

በሕንድም የምርት መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ ሚሊዮኖች ከረሀብ ከመዳን በተጨማሪ በስንዴ ምርት እራሳቸውን ቻሉ።

የዶክተር ኖርማን ቦርላግ ምርጥ ዘር የምርት እጥረት እና ረሀብ በተከሰቱባቸው ሀገራት እየተላከ፤ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች አጥጋቢ ምርት ማግኘት በመቻላቸው ቢሊዮኖች ከረሀብ መዳን ችለዋል።

በዚህ መልኩ ምርምራቸውን በማካሄድ ቁልፍ ለሆነ ዋና ችግር መፍትሔ ያመጡት ዶክተር ቦርላግ፥ የአረንጓዴው አብዮት አባት ተብለው ተሰየሙ።

1970 በተካሄደው የኖቤል ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ወቅትም "ረሃብ የጦርነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ምንጭ በመሆኑ የተሻሻሉ ዘሮችን በመፍጠር የምግብ ዋስትናን በማምጣት ለሰላም መፈጠር መሰረት ጥለዋል" በሚል ኖቤል የሰላም ሸልማት አግኝተዋል

/ ቦርላግ ከዚህም ሌላ በተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች በርካታ ሽልማትና እውቅና ማግኘት የቻሉ ሲሆን በፈረንጆቹ 2009 ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ምርምራቸውን ቀጥለው ቆይተዋል።
በመጨረሻዎቹ የሕይወት ዘመናቸው በነበሩት  ዓመታት ደግሞ የአካባቢ ጥበቃና  የአረንጓዴው አብዮት መስፋፋትን በመደገፍ ሲሰሩ ኖረዋል።

በዋሲሁን ተስፋዬ