ጥምቀትን በሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ትውፊታዊ በሆነ መንገድ በምታከብረው ጎንደር የተገኙት ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ፣ ጎንደርን በኢትዮጵያዊነት መነጽር ውስጥ ተመልክተዋታል።

ብዙ ተመራማሪዎች እና ተጓዞች ስለጎንደር ብዙ ጽፈዋል፤ ደግሞም እፁብ ድንቅ ብለው ተገርመዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ስለጎንደር ህዝብ ከተናገሯቸው ብለው አራት ጉዳዮችን ሰንዝረዋል።
አንደኛው አሉ ፕሬዚዳንቱ “የጎንደር ህዝብ እንደ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሰው ልጅ ከበሬታ፣ ፍቅር እና ሕይወት ያለው እና ለእነዚህም የሚጨነቅ ሰው ወዳድ በመሆኑ አባቶች ይህን በጎ እሴት ማስቀጠል ይገባል” ብለዋል።
ሁለተኛው “የኢትዮጵያዊነት መገለጫው የተረጋጋ፣ ስክነት እና አስተውሎት ያለው መሆኑ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ በትዕግስት እና በአርምሞ ካሰበበት መድረስ የሚችል ትውልድ እንዳላት በማስታወስ፣ ይህንንም የመድህን መንገድ እንከተል እና እናለማው ዘንድ ፀሎታችሁ አይለይን” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
ሦስተኛው ፕሬዚዳንቱ ያነሱት ሃሳብ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ እውነትን ይወዳል፤ ለሀቅ እና ኢትዮጵያዊነት ማዕተብ ተገዥ ነው። ኢትዮጵያዊነት ከፍ ስለሚያደርግ በሁለት እግራችን እንድንቆም አስችሎናልና ይህ ጽናት እንዳይለያችሁ አደራ እላለሁ” ብለዋል።
አራተኛው “ሕዝባችን አስተዋይ፣ ትዕግስተኛ እና በጅግንነት ውስጥ ቻይነት ያለው በመሆኑ ዛሬን ሳይሆን ነገን ያያል፤ አርቆ ማስተዋልን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም መመልከት ታላቅ በረከት ስለሆነ ለእናንተም ለኢትዮጵያ ጽናትም ሲባል ይህንን አጽንታችሁ መያዝ የተገባ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ የመንግሥትን ዋጋ ያውቃል፤ የመንግሥት ሥርዓት ያለው ነው፤ አዲስ ስሪት ሀገር አይደለም። በየዘመኑ እናጎሳቁለዋለን እንጂ በሺህ ዓመታት የሚጠቀስ የመንግሥትነት ታሪክ፣ እውቀት እና ልህቀት ያለው ሀገር ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
መንግሥት ካልጠነከረ አበሳው ብዙ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህን አበሳ አዋኪዎች ቢሸከሙት ጥሩ ነበር ግን የሚደርሰው ለህዝብ በመሆኑ የጽናት እና የአስተውሎት መንገድን እንከተል በማለት አስገንዝበዋል።