Search

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የብልጽግና ምልክት ናት፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ መጋቢት 16, 2018 147

አዲስ አበባን ማዕከል አድርጎ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያ የብልጽግና ማሳያ ምልክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪደር ልማትን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ፤ "ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ባህል ሆኖ የውጭ ሰው ካልነገረን በስተቀር ከውስጥ የሚነገረውን የመቀበል ዝንባሌያችን ዝቅ ያለ ነው፤ አሁን ግን የአዲስ አበባን ውበት የማይመሰክር ያለ አይመስለኝም" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መቀየር የውበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን ገጽታ የመገንባትና የኢኮኖሚ ዕድገትን የማፋጠን ስትራቴጂያዊ እርምጃ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የዘንድሮ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ የገቢ ምንጭ እየሆነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አንድ እንግዳ አዲስ አበባን ወዶ በአድናቆት ከተመለከተ፣ እንደ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ እና ባሕር ዳር ያሉ ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት እንደሚነሳሳም ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ ማማሯና ሰፊ ሕዝብ ያላት ከተማ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች አካባቢዎች ልማትም እንደ መሸጋገሪያ የምታገለግል በመሆኗ፤ ከተማዋ ከኢኮኖሚ ዕድገት አንጻርም በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሏት አብራርተዋል።

በኮሪደር ልማት ንጽሕናው የተጠበቀ፣ ያማረና ዘላቂ የሆነ ሥነ-ምህዳር መፍጠር በማደግ ላይ ያሉ የሁሉም ሀገራት ሕልም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ ያደጉ ሀገራትም ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸው በአጽንኦት ተናግረዋል።

በሃይማኖት ከበደ

#Ethiopia #corridordevelopment #urbancorridor #urbandevelopment #AbiyAhmed