ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያሳረፈና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክንውን ሆኖ ተመዝግቧል።
"ይህንን ምርጫ ምን ልዩ አደረገው? ለሀገራችንስ የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው?" ብለን ስንጠይቅ፣ ምላሹን የምናገኘው በሕዝብ ተሳትፎው አስደናቂ ስፋት፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በግል ዕጩዎች ጠንካራ ተሳትፎ፣ እንዲሁም ሥርዓቱ ባሳየው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ውስጥ ነው።
የዘንድሮውን ምርጫ ትርጉም በውል ለመረዳት፣ በተለይም ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ማነጻጸር የዴሞክራሲያዊ ባህላችንን ጉልህ የእድገት ለውጥ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የሕዝብ ተሳትፎ እና ዲሞክራሲያዊ መነቃቃት
በዘንድሮው ምርጫ የታየው የሕዝብ መነቃቃትና የነቂስ ተሳትፎ ከማንኛውም ጊዜ የተለየ እና የጎላ ነበር። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መረጃ መሰረት፡-
ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመራጭነት ካርድ ወስደዋል።
የምርጫ ካርድ ከወሰዱት ዜጎች ከ94-99 በመቶ በላይ የሚሆኑት በምርጫው ዕለት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
በመላው ሀገሪቱ 1 ሺህ 139 የምርጫ ክልሎች እና 52 ሺህ ገደማ የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው አገልግሎት ሰጥተዋል።
ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መምረጡ፣ ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎትና እምነት ያሳያል።
ይህ ከፍተኛ ቁጥር ከቀዳሚው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን እና የሀገሪቱን እጣ ፈንታ በካርዱ የመወሰን ጽኑ ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያረጋገጠበት ታላቅ ማሳያ ነው።
የፖለቲካ ምህዳሩ መከፈት እና የተወዳዳሪዎች ስፋት
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ይበልጥ ልዩ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ የተወዳዳሪዎች ብዛትና የፖለቲካ አማራጮች መስፋፋት ነው።
በዘንድሮው ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል።
በድምሩ 10,438 የፖለቲካ ፓርቲና የግል ዕጩዎች ቀርበው ተወዳድረዋል።
ይህ ቁጥር የሚያመለክተው የፖለቲካ ምህዳሩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መከፈቱን፣ መንግስትና የሀገሪቱ ተቋማት ፍትሃዊ የውድድር ሜዳ ለመፍጠር ያሳዩትን ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም የተፎካካሪ ኃይሎች በስፋት ወደ ምርጫው መግባታቸውን ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የግል እጩዎችም በነፃነት መወዳደር መቻላቸው፣ ዲሞክራሲያዊ ውድድር በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስር እየሰደደ መምጣቱን ያመላክታል።
ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር፣ የዘንድሮው ምርጫ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በአንድነት አቅፎ፣ ከ10 ሺህ በላይ እጩዎችን አሳትፎ፣ ተፎካካሪዎች በስፋት አሸንፈው ወደ ምክር ቤት የገቡበት በመሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ ምን ያህል እንደጎለበተ ያሳያል።
የምክር ቤቶች ስብጥር፡ የብዝሃነት እና የአካታችነት መስተዋት
የዘንድሮው የምርጫ ውጤት ፓርላማውን (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን) እና የክልል ምክር ቤቶችን እውነተኛ የብዝሃነት መስተዋት አድርጓቸዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች ወንበር ማግኘታቸው የሀሳብ ብዝሃነት በተቋም ደረጃ እየተረጋገጠ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።
አጠቃላይ የፓርላማ ውጤቱን ስንመለከት፦
ብልጽግና ፓርቲ፡ 438 መቀመጫዎችን አግኝቷል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች፡ በድምሩ 40 መቀመጫዎችን ማግኘት ችለዋል።
የግል ዕጩዎች፡ 8 ዕጩዎች አሸንፈው ወደ ፓርላማ ገብተዋል።
በየክልሉ እና ከተማ መስተዳድሮች የታየው የተፎካካሪዎች እና የግል እጩዎች ስኬት የዲሞክራሲን ትርጉም ይበልጥ የሚያጎላ ነው።
አማራ ክልል፡ ምርጫ ከተካሄደባቸው 130 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ ተፎካካሪዎች 13 መቀመጫዎችን (አብን 6፣ አዲህን 3፣ እና ሌሎችም 4) ማሸነፍ ችለዋል።
ኦሮሚያ ክልል፡ 5 የግል ዕጩዎች እና 1 የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዕጩ ማሸነፋቸው የፖለቲካ ምህዳሩ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ያሳያል።
ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ከ45ቱ መቀመጫዎች 10ሩን (ኢዜማ 7፣ ሌሎች 3)፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ደግሞ ከ33ቱ 5ቱን (ኢዜማ 2፣ ሌሎች 3) ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች አሸንፈዋል።
አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና ሲዳማ፡ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከ23ቱ 3ቱን (ኢዜማ 2፣ የግል 1)፣ በሶማሌ ክልል ኦብነግን ጨምሮ ተፎካካሪዎች 3 መቀመጫ ሲያገኙ፣ በሲዳማ ክልል ደግሞ መድረክ 3 ወንበሮችን አግኝቷል።
ይህ የውጤት ስብጥር የሀገሪቱ የፓርላማ ወንበር የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ ጫፎች የመጡ የብዙሃን ድምፅ መፍለቂያ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ባጠቃላይ ሲታይ፣ ምርጫ 2018 (7ኛው ጠቅላላ ምርጫ) ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ግንባታ ላይ የምታደርገውን ጉዞ በብዙ ርምጃ ወደፊት ያራመደ፣ ለተፎካካሪ ኃይሎች ሰፊ በር የከፈተ እና የህዝብን ድምፅ ያከበረ ምርጫ ነው።
መንግሥት ያሳየው አስደናቂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሰጠው ድምፅ፣ እንዲሁም የግል ዕጩዎችና በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በስፋት ወደ ፓርላማ እና የክልል ምክር ቤቶች መግባታቸው ይህን ምርጫ ታሪካዊ እና ልዩ ያደርገዋል።
ይህ የዴሞክራሲ ድል ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የፖለቲካ መረጋጋት፣ ብሔራዊ መግባባት እና የሀሳብ ብዙሃነትን ወደሚያስተናግድ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እያሸጋገራት መሆኑን የሚያሳይ የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ