Search

ቁጥሮች ምን ያወራሉ?

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 58

ቁጥሮች ዝም ብለው በወረቀት ላይ የሰፈሩ ደረቅ ሂሳቦች አይደሉም። ቁጥሮች ዝም አይሉም፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያወራሉ!  የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ቁጥሮች የኢትዮጵያን የልብ ትርታ፣ የሕዝቧን የነፃነት አየር ወደ ውስጥ የመሳብ ጉጉት እና የዲሞክራሲን ፅንሰት የሚያበስሩ ሕያው ምስክሮች ናቸው። ቁጥሮቹ የትናንቱን ፈተና አልፎ ለነገው ብሩህ ተስፋ የተነሳውን ሕዝብ የድል ጉዞ በትረካ መልክ አፍ አውጥተው ይናገራሉ።

May be a graphic of text

እውነት ቁጥሮች ምን ያወራሉ? "ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመራጭነት ካርድ ወሰዱ" የሚለው አኃዝ፣ አንድ ታላቅና ጀግና ህዝብ የሀገሩን እጣ ፈንታ በገዛ እጁ ለመወሰን ያደረገውን ጽኑ የዜግነት ቃል ኪዳን በከፍተኛ ድምጽ ያወራል።

"ከ96.2 በመቶ በላይ የሚሆኑት መራጮች በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን ሰጡ" ሲባል ደግሞ፣ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ በፀሐይ ንዳድና በዝናብ ካፊያ ሳይበገር፣ በ1 ሺህ 139 የምርጫ ክልሎች እና በ52 ሺህ ገደማ የምርጫ ጣቢያዎች በረጅም ሰልፍ ተሰልፎ ሀገሩን ያፀናውን ጀግና ሕዝብ ታሪክ ይተርካል።

ይህ ቁጥር የኢትዮጵያውያንን ፅኑዕ ፍላጎት፣ የማይበገር አገራዊ ፍቅር እና ሰላማዊ የትግል አውድማ ላይ የተቀዳጁትን አንጸባራቂ ድል የሚያንጸባርቅ የጀግንነት ሐውልት ነው። የህዝቡ ድምጽ የሀገርን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ ማህተም ሆኗል።

 

ቁጥሮች የመንግሥትን እጅግ ታላቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነትም በጉልህ ይናገራሉ። 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 10,438 የፖለቲካ ፓርቲና የግል ዕጩዎች የተወዳደሩበት አውድማ መፈጠሩ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ በሩን ወለል አድርጎ መክፈቱንና የዲሞክራሲ በር መገንጠሉን ያሳያል።

May be a graphic of text

ከእነዚህ ውስጥ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 8 የግል ዕጩዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ማሸነፍ መቻላቸው፣ ከቃላት ያለፈ የተግባር ጀግንነት ማሳያ ነው። ብልጽግና ፓርቲ 438 መቀመጫዎችን ሲያገኝ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች 37 ወንበሮችን ማሸነፋቸው፣ ከመሸናነፍ የጠባብ ፖለቲካ ትርክት ወጥቶ በጋራ አብሮ ማሸነፍን የሰበከ፣ የብዙኃን ድምፅ የተከበረበት እውነተኛ የዲሞክራሲ ድል ነው።

ይህ የቁጥር ድምር መንግሥት ለብዝኃነት ያሳየውን ወደር የለሽ ክብርና ለሀገር ግንባታ የከፈለውን ፅኑ የተግባር ቁርጠኝነት በትክክል ይተርካል።

ወደ ታችኛው የሥልጣን እርከን ስንወርድም ቁጥሮቹ የድል ዜማቸውን በህብረ-ዜማ ያሰማሉ። በሐረሪ 99 በመቶ፣ በኦሮሚያ እና ሲዳማ 97 በመቶ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ 96 በመቶ፣ እንዲሁም በአማራ 95 በመቶ እና በሶማሌ 94 በመቶ የታየው ከፍተኛ የመራጮች ተሳትፎ፣ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር በዲሞክራሲ ጎዳና ላይ በአንድ ልብ መቆማቸውን ያረጋግጣል።

በአዲስ አበባ 10 የተለያዩ ፓርቲዎች፣ በአማራ ክልል 9፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሌ 7 ፓርቲዎች በምክር ቤት መወከላቸው፣ ሀገራችን የብዝኃነት ውበት የደመቀባት፣ የተለያዩ ሀሳቦች አብረው የሚኖሩባት የጋራ ቤት መሆኗን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ስለዚህ፣ የዘንድሮው ምርጫ ቁጥሮች ዝም አይሉም፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያወራሉ! ስለ ኢትዮጵያ የፀናች ሀገረ መንግሥትነት፣ ስለ መንግሥት ልባዊና ጥልቅ ቁርጠኝነት፣ እና ስለ ሕዝቡ ወደር የለሽ ሰላማዊ ጀግንነት በኩራት ይዘምራሉ። እነዚህ ቁጥሮች የህዝብን ድምፅ ወደ ውብ የዲሞክራሲ ዜማ የቀየሩ፣ የልዩነትን ግድግዳ አፍርሰው የአንድነትን ድልድይ የገነቡ ታሪካዊ ዐሻራዎች ናቸው።

በእርግጥም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ ካርዱ ያጻፈው ይህ የቁጥር ትርክት፣ ለትውልድ የሚተላለፍ የድልና የጀግንነት ተውኔት ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ