Search

የኢትዮጵያዊያን የተለያየ ድምፅ በአንድ አዳራሽ፦ የብዝኃነት ፖለቲካ በተግባር

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 56

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ማጠቃለያ ውጤት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
በምርጫው ሂደት 17 የተለያዩ ርዕዮተ-ዓለም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 8 የግል ተወዳዳሪዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤቶች ወንበር ማሸነፍ መቻላቸው በሀገራችን ለረጅም ዘመናት የቆየውን የአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነት ባህል ሙሉ በሙሉ ያስቀረ ነው።
ይህ ውጤት ምክር ቤቶቹ የአንድ ወገን የውሳኔ ማሳለፊያ ከመሆን አውጥቶ፣ በርካታ ድምፆችና የሐሳብ ብዝኃነት በተግባር የሚስተናገዱበት ንቁ መድረክ ያደርገዋል።
ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተወከሉ የፓርቲና የግል ተወዳዳሪዎች በምክር ቤቶቹ በመገኘታቸው፣ ሕግ አውጪው አካል በአስፈጻሚው መንግሥት የሚወጡ አዋጆች፣ በጀቶችና ፖሊሲዎች ጠንካራ ክርክርና ምርመራ እንዲያደርግባቸው ዕድል ይፈጥራል። ይህ አካሄድ የ«ቼክ ኤንድ ባላንስ» ሥርዓትን በማጎልበት በሀገራችን አስተማማኝ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያደርጋል።
በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የነበረውን የምርጫ ሥርዓት አለመተማመን በመቅረፍ፣ የፖለቲካ ለውጥ ማምጫው ብቸኛው መንገድ ሕጋዊና ሰላማዊ ምርጫ ብቻ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ይህም የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸውን እምነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል።
ኢትዮጵያ የተለያየ ፍላጎት፣ ባህል፣ የታሪክ እይታና የኢኮኖሚ ጥያቄ ያላቸው ማኅበረሰቦች ስብስብ እንደመሆኗ የእነዚህ 17 ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች መመረጥ የኅብረተሰቡ የሐሳብ ብዝኃነት በሕግ ደረጃ እንዲወከልና የትኛውም የሕዝብ ድምፅ ሳይገለል በከፍተኛው የሥልጣን ማማ ላይ «በጠረጴዛ ዙሪያ» እንዲደመጥ ያደርጋል።
አገራዊ የሆኑ ትልልቅ የሕግ ማሻሻያዎችና የፖሊሲ አቅጣጫዎች በሚረቁበት ጊዜ የተፎካካሪዎችንና የነፃ ተወካዮችን ሐሳብ ለማካተት ያስችላል። ይህ ሂደት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እምብዛም ያልተለመደውን ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን በከፍተኛ ሁኔታ ያዳብራል።
ለዚህ ታሪካዊ ስኬት መገኘት ደግሞ በምርጫው ሂደት የተሳተፉ 42 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎች ያሳዩት ከፍተኛ ቁርጠኝነትና የሰላማዊ ፉክክር መንፈስ ደማቅ አድናቆት አስገኝቶላቸዋል።
እነዚህ ወገኖች በየደረጃው የነበረውን የሀሰት መረጃ፣ ፕሮፓጋንዳና ልዩ ልዩ የሀሰት ወጀቦችን በጽናት በመቋቋም፣ ለሰላማዊ የሃሳብ ውድድር እና ለሕግ የበላይነት መከበር ያሳዩት ፅናት በሀገራችን የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የፓርቲዎቹና የዕጩዎቹ በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ የመወዳደር ስነ-ምግባር የቆየውን የአንድ ወገን የፖለቲካ ስብስብ ባህል በማስቀረት፣ በተግባር የተደገፈ የሀሳብ ብዝኃነት እንዲጎለብትና የዜጎችን ሉዓላዊ ሥልጣን እንዲረጋገጥ አድርጓል።
ይህ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብስለትና የሰላማዊ ትግል ቁርጠኝነት፣ ምርጫው በሀገር ውስጥ ሰላማዊና አካታች ሆኖ እንዲጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ክብርና ገፅታ በዓለም አቀፍ መድረክ ወደ አዲስ ከፍታ አሸጋግሮታል።
ባጭሩ ይህ ውጤት የሚያሳየው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካለፈበት የ«እኔ ብቻ» አካሄድ ወጥቶ፣ ልዩነቶችን ይዞ በአንድነት ወደመሥራት እና ወደ ብስለት እየተሸጋገረ መሆኑን ነው።
በበረከት ሽመልስ