ምርጫዎች በአብዛኛው የፖለቲካ ኃይሎች የሥልጣን ሽግግር የሚረጋገጥባቸው የፉክክር መድረኮች ናቸው።
ሆኖም የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ መደበኛ የምርጫ ትርጓሜ እጅግ የላቀና የገዘፈ ትርጉም አለው።
ይህ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመሸናነፍ በዘለለ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ቆሞ ሀገሩን ያጸናበት፣ የዲሞክራሲ መሠረቱን ያደላደለበትና ብሔራዊ ህልውናውን ያረጋገጠበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

በዘንድሮው ምርጫ ጎልቶ የታየው ዋነኛ እውነት፣ ሕዝቡ ሀገርን በካርዱ የማጽናት ጽኑ ፍላጎቱ ነው።
ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመራጭነት ካርድ በመውሰድ እና ከ96.2 በመቶ በላይ የሚሆኑት በምርጫው ዕለት ድምፃቸውን በመስጠት ያሳዩት ተሳትፎ፣ ከመራጭነት ተግባር ባለፈ "ሀገሬንና አንድነቷን እጠብቃለሁ" የሚል የዜግነት ቃል ኪዳን ነው።
በመላው ሀገሪቱ በተቋቋሙ 1 ሺህ 139 የምርጫ ክልሎች እና 52 ሺህ ገደማ የምርጫ ጣቢያዎች ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሰጠው ድምፅ ኢትዮጵያ በፅናትና በተስፋ ወደፊት እየተራመደች መሆኗን ለዓለም ያወጀ ታሪካዊ ክስተት ነው።
እያንዳንዱ መራጭ የሰጠው ድምፅ፣ የፖለቲካ ፓርቲን ከመምረጥ ባሻገር ሀገረ-መንግሥቱን (State-building) የማጽናት ታላቅ ኃላፊነት የተወጣበት ድርጊት ነበር።
አሸናፊና ተሸናፊ በሚል ጠባብ ትርክት ፋንታ፣ ምርጫው የጋራ ሀገር ግንባታ ማሳያ ሆኗል። በምርጫው ከተወዳደሩት 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 17ቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ማሸነፋቸው የሀገሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያበስራል።
የፓርላማ ስብጥር፡ ብልፅግና ፓርቲ 438 ወንበሮችን ሲያሸንፍ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች 37፣ እንዲሁም 8 የግል ዕጩዎች ወደ ፓርላማ መግባታቸው የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ አካታች መሆኑን ይመሰክራል።
የክልል ምክር ቤቶች መነቃቃት፡ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች በክልል ምክር ቤቶች ውስጥ መወከላቸው፣ ዲሞክራሲ በታችኛው የሥልጣን እርከን ላይ ይበልጥ እንዲጠልቅ ዕድል የፈጠረ ነው።
ይህ የሚያሳየው ምርጫው የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ ጫፎች የመጡ የብዙሃን ድምፅ መፍለቂያ መሆኑን ነው። ዲሞክራሲ የአንድ ወጥ ዜማ መድረክ ሳይሆን፣ የብዙ የተለያዩ ድምፆች ውብ ቅንብር የሚፈጥረው አገራዊ ስምምነት መሆኑ በዚህ ምርጫ በተግባር ተረጋግጧል።
የ10,438 የፖለቲካ ፓርቲና የግል ዕጩዎች በምርጫው መሳተፍ፣ መንግሥትም ሆነ አጠቃላይ ሥርዓቱ ለዲሞክራሲ ግንባታ ያሳዩትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ይመሰክራል። ከዚህ ቀደም የነበሩ የፖለቲካ ምህዳር ጥበቦችን በመስበር፣ ከተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የሕዝብን ድምፅ ማግኘት መቻላቸው፣ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ብሩህ ገፅታ ነው።
የክልል ምክር ቤቶች የአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ የሚሰበሰቡባቸው ሳይሆኑ፣ የተለያዩ የህዝብ ጥያቄዎችና አማራጭ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው የውይይት መድረኮች እንዲሆኑ በር ተከፍቷል። ይህ አካታችነትና የብዙኃን ድምፅ ተሰሚነት፣ ለጠንካራ ፌዴራላዊ ሥርዓትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የማይተካ ሚና አለው።
በማጠቃለልም፣ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት የሚያረጋግጠው፣ የኢትዮጵያ ፅናት በብዙሃን ድምፆች መከበርና መደመጥ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው።
የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች በፓርላማ መገኘት ለነገዋ የበለፀገችና የተረጋጋች ኢትዮጵያ የጸና የመሠረት ድንጋይ ነው። ይህ ምርጫ "ከመሸናነፍ በዘለለ" መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ በመቆም ዲሞክራሲያዊ አገሩን ያጸናበት ደማቅ የታሪክ ማኅተም ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ