የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋራ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትሩ በለንደን የአየር ንብረት እርምጃ ሳምንት ማስጀመሪያ ላይ በለንደን ስቶክ ኤክስቼንጅ በመገኘት የዕለቱን ግብይት በይፋ ከፍተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በሳምንቱ እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በለንደን የአየር ንብረት እርምጃ ሳምንት ቆይታቸው፣ ሁሉም አካላት ያላቸውን ሀብት፣ እውቀትና የጋራ አቅም በማስተባበር ለመላው ዓለም ሊሰሩ የሚችሉ ብልህ መፍትሔዎችን ማምጣት እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በየዓመቱ በሰኔ ወር የሚካሄደው የለንደን የአየር ንብረት እርምጃ ሳምንት፤ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት እርምጃዎችን ለማጠናከር ሲባል ባለሀብቶችን፣ ባንኮችን፣ የንግድ ተቋማትን እና የፖሊሲ አውጭዎችን በአንድ ላይ የሚያገናኘ መድረክ ነው።
በለንደን ዛሬ በተመጀመው በዚህ ኩነት ከከፍተኛ ጉባኤዎች እስከ ማኅበረሰብ አቀፍ ተነሳሽነቶች ያሉ የተለያዩ የክንውን መርሃ-ግብሮችን የሚደረጉ ሲሆን፤ እንደ ፋይናንስ፣ ኢነርጂ፣ ፖሊሲ እና ተፈጥሮ ያሉ አበይት ርዕሰ-ጉዳዮች ይዳሰሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።