ለእነርሱ አሰብ ከተማ ብቻ አይደለችም፤ የልጅነት ትዝታቸው የተቀበረባት፣ የቀይ ባሕር ማዕበልን እየታገሉ የዋኙባት እና ማንነታቸውን ያገኙባት የትውልድ ምድር እንጂ።

ዛሬ በባቲ ከተማ የሚኖሩ የቀድሞ የአሰብ ነዋሪዎች ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የተወለዱባት፣ ያደጉባት እና የቀለም ትምህርት የቀሰሙባት አሰብ እንደምትናፍቃቸው በስሜት ይገልጻሉ።
አሰብን ለቀው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በውስጣቸው የከበደ ቁጭት እንዳደረባቸው የሚናገሩት እነዚህ ተወላጆች፣ በተለይም ከተማዋ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ መነጠሏ ዛሬም ድረስ እንደሚያንገበግባቸው ሳይደብቁ ይናገራሉ።

ወደ ኤርትራ እና አፋር ለመሸጋገር ወሳኝ የንግድ ቀጣና የሆነችው ባቲ ከተማ ለአሰብ ነዋሪዎች ትልቅ ትዝታ ያላት ስፍራ ናት።
በተለይም ታዋቂው የባቲ "የሰኞ ገበያ" የሁለቱን አካባቢዎች ነዋሪዎች ከማገናኘት ባለፈ፣ የንግድ ልውውጡ እስከ የመን ድረስ የሚዘረጋ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደነበር ያስታውሳሉ።

አሰብ፣ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር በፍጹም የማይነጣጠሉ የታሪክ እና የተፈጥሮ አካላት መሆናቸውን የሚመሰክሩት ነዋሪዎቹ፣ በቀይ ባሕር ሞገድ ውስጥ እየዋኙ ያደጉበትን ያን ወርቃማ ጊዜ በናፍቆት ያወሳሉ።
በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ አሻጥር ምክንያት ካፈሩት ሀብትና ንብረት በላይ የትውልድ ምድራቸውን ማጣታቸው ቢያሳዝናቸውም፣ ተስፋ ግን አልቆረጡም።

አሰብ ወደ እናት ሀገሩ ተመልሶ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የሚኩራሩበትን የትውልድ ስፍራ ማሳየት ትልቁ ምኞታቸው እንደሆነ ገልጸው፤ በምንም ሁኔታ ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባው ሀቅ "አሰብ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ሀቅ" መሆኑን በጽኑ አቋም አረጋግጠዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ