የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የአንዲት ታላቅ ሀገር የህልውና፣ የፍትሕ እና የዘላቂ ኢኮኖሚ ደህንነት ጉዳይ ነው። ዛሬ ላይ ይህን አንገብጋቢ ሀገራዊ ፍላጎት ለመመለስ የሚኬድበት መንገድ በዜሮ ድምር (Zero-sum game) የፖለቲካ ሸፍጥ እና ጉልበት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ "መደመር" በሚለው እሳቤ ላይ የቆመ ነው።
የባሕር በሩ ይደመራል፤ ይህ መደመር ግን የሌላውን ሉዓላዊነት በመጋፋት አሊያም በማስገደድ መንጠቅ ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ የጋራ ተጠቃሚነትን (Win-Win)፣ የወል እውነትን ማዳበርን እና የላቀ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ማረጋገጥ ነው።
የመረጃ እና የኢኮኖሚ እውነታዎች ሲፈተሹ
ጉዳዩን በመረጃ ስንመዝነው፣ የባሕር በሩ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የእስትንፋስ ያህል ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን።
· የህዝብ ብዛት እና ገበያ፡- ከ130 ሚሊዮን በላይ ብርቱ እና ወጣት ህዝብ ያላት፣ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚውን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) የያዘች ሀገር፣ የባሕር በር አልባ ሆና መቀጠሏ ተፈጥሯዊም ኢኮኖሚያዊም ግድፈት ነው።
· የሎጂስቲክስ ወጪ፡- ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ እና ተያያዥ የሎጂስቲክስ ወጪዎች የምታወጣው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ውድ ሀብት፣ ብሔራዊ የዕድገት ጉዟዋን ክፉኛ የሚፈታተን ማነቆ ነው።
· የንግድ ጥገኝነት፡- ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የገቢ እና ወጪ ንግዷ በተወሰኑ ኮሪደሮች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑ፣ ከሀገራችን የህዝብ ቁጥር ዕድገት እና ከታቀደው የኢንዱስትሪ ሽግግር ጋር በፍጹም የሚመጣጠን አይደለም።
የመደመር እሳቤ እና የአፍሪካዊ ልማት ትስስር
ከመደመር እሳቤ አንፃር፣ ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለው ጥያቄ "ኑ አብረን እንደግ፤ የኔ ግዙፍ የገበያ አቅምና የናንተ የውኃ በር ተደምሮ የቀጣናውን ህዝብ ከድህነት ያውጣ" የሚል የሰለጠነ የትብብር ጥሪ ነው። የመደመር ፍልስፍና መነሻው ነባር አቅሞችን አዋህዶ፣ የጎደለውን ሞልቶ፣ በጋራ ማደግ ነው። የባሕር በሩ ወደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሲደመር፣ ቀጣናዊ ትብብርና ወንድማማችነትን በላቀ ደረጃ ያሰፋል።
ይህ እሳቤ የአፍሪካን ሕዳሴ እና የኢኮኖሚ ትስስር በተግባር ለማሳየት የሚያስችል ኃይለኛ መሳሪያ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በወደብ፣ በመንገድ፣ በባቡር እና በኃይል አቅርቦት ሲተሳሰሩ፣ ሰው ሰራሽ የቅኝ ግዛት ድንበሮች ያመጡት መከፋፈል ይሽራል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ማዕቀፍ ውስጥ ትልቁን ትርጉም የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን የራሳቸውን የልማት ጥያቄ በራሳቸው አቅም የመፍታት ብቃታቸውን የሚያረጋግጥ ፓን-አፍሪካዊ ራዕይ ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ፖለቲካ የዕዳ ሸክም (Liability) ወይስ የልማት ሞተር (Asset)?
በዚህ ቀጣናዊ ስሌት ውስጥ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቁ ሀቅ የኢትዮጵያ ደካማ መሆን ለጎረቤቶቿ የሚያመጣው መዘዝ ነው። 130 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሀገር በድህነት እና በኢኮኖሚ መታፈን ውስጥ ከቆየች፣ የቀጣናው ሰላም፣ ደህንነት እና መረጋጋት አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው።
ተፈጥሯዊ የመተንፈሻ በሯ የተዘጋባት እና ከድህነት ጋር የምትታገል ኢትዮጵያ፣ ለጎረቤቶቿ ብሎም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእዳ ሸክም እና የተደራራቢ ቀውስ ምንጭ መሆኗ አያጠራጥርም። የሃብት እጥረት እና የኢኮኖሚ መቆለፍ የሚያስከትለው የህዝብ ፍልሰት እና የፀጥታ ስጋት፣ የሌላውን ሀገር ደጃፍ ማንኳኳቱ የማይቀር የተፈጥሮ ሕግ ነው።
በተቃራኒው፣ በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያ ማደግ እና መበልፀግ ስትችል የቀጣናው የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ዋስትና ትሆናለች። የባሕር በር አግኝታ ኢኮኖሚዋ ሲያገግም፣ አካባቢዋን በኢንቨስትመንት እና በንግድ ልውውጥ ጎትታ ታወጣለች። የኢትዮጵያ ብልፅግና የጎረቤቶቿም ብልፅግና ነው።
የባሕር በሩ ወደ ኢትዮጵያ ይደመራል። ይህ መደመር ግን የጥላቻን እና የጥርጣሬን ግድግዳ የሚያፈርስ፣ የወል እውነትን የሚያነግስ፣ የጋራ ፀጥታን የሚያረጋገጥ እና የቀጠናውን ህዝቦች በተስፋ ብርሃን በደመቀ የብልፅግና ጠረጴዛ ዙሪያ የሚያሰባስብ ነው። መደመር ከሌላው መቀነስ ሳይሆን ማብዛት መሆኑን፣ ማግለል ሳይሆን ማካፈል መሆኑን የባሕር በሩ ጥያቄ በተግባር ያረጋግጣል።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ