Search

"ቁሳዊ ልማት በሰው ኃይል ግንባታ መጀመር አለበት" የሚለውን እሳቤ እየደገፈ ያለው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ

ዓርብ መጋቢት 18, 2018 169

ኢትዮጵያ "ቁሳዊ ልማት በሰው ኃይል ግንባታ መጀመር አለበት" የሚለውን ቀዳሚ እሳቤ መሠረት በማድረግ፣ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን በስኬት አጠናቃ ወደ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይ ተሸጋግራለች። 

ይህ ሀገራዊ ራዕይ በአራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የቆመ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ያደረጉት የ"አምስት ሚሊዮን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ የዚህ ታላቅ ጉዞ የጀርባ አጥንት ተደርጎ ይወሰዳል።

በኢፌዴሪ መንግሥት እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በትብብር የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፣ ሀገራችንን ቀደም ሲል ከነበረው ልማዳዊ የኢኮኖሚ መዋቅር በማውጣት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማስፈንጠር የተወሰደ ታሪካዊ እና ስልታዊ እርምጃ ነው።

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ዓላማ ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ የበለጸገች እና የዕውቀት ውጤቶችን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ ሀገር ማድረግ ሲሆን፣ ሥልጠናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ አራት ቁልፍ የቴክኖሎጂ ዘርፎችን ያቀፈ ነው።

ኢኒሼቲቩ ወጣቶችን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ዴቨሎፕመንት፣ በዳታ ሳይንስ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፎች በማሠልጠን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እያረጋገጠ ይገኛል። 

የዳታ ሳይንስ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ክህሎቶች ከፈጠነው ዘመን ጋር የሚሄዱ እና መረጃን መሠረት ያደረጉ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመስጠት እና ከዓለም የቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር ለመራመድ የሚያስችሉ ወሳኝ ክህሎቶች ናቸው።

የዚህ ግዙፍ ሥልጠና ስልታዊ ፋይዳ ወደፊት ለሚገጥመን ውስብስብ የዲጂታል ዓለም የበቃ እና የተዘጋጀ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ያተኩራል።

ሠልጣኞች ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በአካል ሀገራቸው ሆነው በየትኛውም የዓለም ክፍል ላለ ቀጣሪ ሥራቸውን በማከናወን ለሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙበትን የዲጂታል የሥራ (Digital Labor) ዕድልን ይፈጥርላቸዋል።

ይህም የሀገር ውስጥ ድርጅቶችን በቴክኖሎጂ የሚደግፍ እና ሥራ ፈጣሪ የሚሆን ትውልድ በመፍጠር የተቋማትን አሠራር ለማዘመን ትልቅ ዕድል ነው።

ኢኮኖሚያዊ ስሌቱን ስንመለከተው፣ ሥልጠናውን እንዲወስዱ በግብ ከተያዘው አምስት ሚሊዮን ሰዎች መካከል አሥር በመቶዎቹ ብቻ በዓለም አቀፍ ገበያ ተሰማርተው በወር በአማካይ 500 ዶላር ገቢ ቢያገኙ፣ በዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይቻላል። 

ይህንኑ ግብ ለማሳካት በ2017 ዓ.ም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሥልጠናውን በመከታተል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የምስክር ወረቀት ማግኘት ችለዋል።

ዛሬ ላይ ይህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን፣ በርካታ ኮደሮችም ወደ ሥራው ዓለም በመቀላቀል በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛሉ።

የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የወጣቱን የፈጠራ ብቃት ወደ ኢኮኖሚያዊ እሴት የሚቀይር ድልድይ በመሆን የነገዋን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ 

#DigitalEthiopia #5MillionCoders #TechInnovation #Ethiopia #EBC