በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው አንትሮፒክ (Anthropic)፣ ኮፊሸንት ባዮ (Coefficient Bio) የተባለውን የባዮቴክኖሎጂ ስታርታፕ በ400 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ባለው አክሲዮን መግዛቱን ይፋ አድርጓል።
ይህ እርምጃ አንትሮፒክ የሕክምና ሳይንስን እና የመድኃኒት ምርምር ሂደትን በኤአይ በመታገዝ በመሠረታዊነት ለመቀየር የሰነቀውን ራዕይ የሚያሳይ መሆኑ ተመልክቷል።
በኒውዮርክ የሚገኘው ኮፊሸንት ባዮ፣ ከተመሠረተ ገና 8 ወራት ቢሆነውም በዘርፉ ባሳየው የፈጠራ ብቃት የቴክኖሎጂ ግዙፎችን ትኩረት መሳብ ችሏል።
ስታርታፑ 10 ሠራተኞች ብቻ ያሉት ቢሆንም፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም አዳዲስ የመድኃኒት ዓይነቶችን በፍጥነት ለመለየት የሚያስችል ሥርዓት መገንባቱ ተገልጿል።
መሥራቾቹ ሳሙኤል ስታንተን እና ናታን ፍሬይ ቀደም ሲል በታዋቂው "ጄኔንቴክ" ኩባንያ ውስጥ በመድኃኒት ምርምር ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ናቸው።
አንትሮፒክ ይህን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰው ለቴክኖሎጂው ብቻ ሳይሆን፣ በዘርፉ ያሉ እጅግ ብቁ ተመራማሪዎችን (Talent Acquisition) ወደራሱ ለመሳብ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኩባንያው በቀጥታ ለባዮሎጂ እና ለሕክምና ምርምር ብቻ የሚያገለግል የኤአይ ሞዴል ለመገንባት መነሣሣቱ፣ እንደ ‘ጉግል ዲፕማይንድ’ እና ‘ንቪዲያ’ ካሉ ተፎካካሪዎቹ ጋር ያለውን የገበያ የበላይነት ለማስጠበቅ የሚረዳው መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ኢትዮጵያ በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ውስጥ ለያዘችው የጤና ዘርፍ ዲጂታላይዜሽን ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
እንደ ኮፊሸንት ባዮ ያሉ የፈጠራ ሐሳቦችን ማበረታታት፣ እንደ የጡት ካንሰር ያሉ በሽታዎችን በጊዜ ለመለየት እና በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት መንገድ ይከፍታል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና እንደ "HEP Assist" ያሉ የጤና ረዳት ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ግኝቶችን በማላመድ ለገጠር ማኅበረሰቦች ትክክለኛ የጤና ውሳኔ ለመስጠት እንደሚረዱ ይጠበቃል።
በአጠቃላይ፣ አንትሮፒክ የወሰደው ይህ እርምጃ የሕክምና ሳይንስ ወደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን (AI Age) በይፋ መሸጋገሩን የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የጤና ሥርዓታቸውን ይበልጥ ለማዘመን ትልቅ መነሣሣትን የሚፈጥር ክስተት ነው።
በለሚ ታደሰ