የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ 7ኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የሚታዘበውን የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ለመምራት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ኬንያታ አዲስ አበባ ሲደርሱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
"ምኞታችን ኢትዮጵያ ጥንካሬዋን እያሳደገች ለአህጉራችን አርአያ ሆና እንድትቀጥል ነው" ያሉት ኬንያታ፣ ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ ለአፍሪካ ትልቅ ድል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የምታከናውነው የዴሞክራሲያዊ ሂደት ታማኝነት በመላው አህጉሪቱ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።

ኬንያታ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ከ37 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 73 የአጭር ጊዜ ታዛቢዎችን ያቀፈ ነው። ቡድኑ የምርጫ ባለሙያዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎችን የያዘ ነው ተብሏል።
ዴሞክራሲን በአፍሪካ ለማጠናከር የአፍሪካ ኅብረት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ኬንያታ፣ የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን "ምርጥ ተሞክሮዎች" ማዳበር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
"የእኛ ተጨባጭ ሁኔታዎች ልዩ ናቸው" ያሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ "ከሌላው ዓለም ሞዴሎችን ገልብጦ መተግር የግድ አስፈላጊ አይደለም። ከራሳችን መማር እና መፍጠር፣ እንዲሁም በመላው አህጉር ጠንካራ ተሞክሮዎችን ማሰራጨት እንችላለን" ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ነገ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ዜጎች ምርጫቸውን በጥበብ እንዲያደርጉ እና ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። "ምርጫው ሰላማዊ እንደሚሆን እና ሕዝቡም ዴሞክራሲያዊ ፍላጎቱን የመግለጽ ዕድል እንደሚያገኝ ትልቅ ተስፋ አለኝ" ያሉት ኬንያታ፣ አሁን የሚጣለው መሠረት ኢትዮጵያ ወደፊት የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች ለመወጣት በምታደርገው ጉዞ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በላሉ ኢታላ