Search

"የኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የምትከፍትበት ዕለት - "ሰኞ ግንቦት 24

እሑድ ግንቦት 23, 2018 50

በቀን መቁጠሪያው ላይ እንደ አንድ መደበኛ ቀን ብትታይም፣ በውስጧ ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን መጻኢ ዕድል በገዛ እጃቸው የሚቀርጹበት ታሪካዊ አጋጣሚን አቅፋ ይዛለች።

ነገ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊዮን በላይ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በማቅናት ድምፃቸውን ያሰማሉ።

ይህ ሂደት የፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ሉዓላዊነት በተግባር የሚገለጽበት እና ዴሞክራሲያዊ መሠረቶች በሕዝብ እጅ የሚረጋገጡበት ታላቅ ሀገራዊ ክስተት ነው።

ለዘመናት በተለያዩ ታሪካዊ ምዕራፎች ያለፈችው ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ሰኞ በአዲስ ተስፋ፣ በከፍተኛ ጉጉት እና በላቀ ሀገራዊ ስሜት ትቀበለዋለች።

ምርጫ ማለት በወረቀት ላይ ምልክት ማድረግ ብቻ አይደለም፤ ስለ ልጆቻችን ነገ፣ ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና በነጻነት የምንወስንበት የዜግነት ከፍተኛ መገለጫ ነው።

የነገዋ ዕለት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ የባለቤትነት ስሜትን የምታረጋግጥ ታሪካዊ ቀን ናት።

ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን፣ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪም ራሱ ሕዝቡ መሆኑን በተግባር የምናሳይበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

ነገ ሕዝቡ በሰላማዊ፣ በነጻ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲያመራ ለዓለም የሚያስተላልፈው ታላቅ መልዕክት አለ፤ ልዩነቶቻችንን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መፍታት የምንችል የበሰልን ሕዝቦች ነን የሚል ክቡር ምስክርነት ነው።

ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ጥረትና ብስለት የራሷን ጉዳይ በራሷ ማስተዳደር እንደምትችል የምታሳይበት ታላቅ አጋጣሚ ነው።

በአፍሪካ ቀንድ የዴሞክራሲ ተምሳሌት ለመሆን የምናደርገውን ጉዞም የሚያጠናክር እርምጃ ነው።

ታሪክ ያስተምረናል፤ ታላላቅ ሀገራት የዛሬው የዴሞክራሲ ከፍታ ላይ የደረሱት በአንድ ጀምበር አይደለም።

በእንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ ቀናት ሕዝቡ በሚያሳየው ብስለት፣ ታጋሽነት እና የሀገር ፍቅር ነው የዴሞክራሲ መሠረቱ እየጠነከረ የሚሄደው።

ስለዚህ የነገዋ ሰኞ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ልጅ የሀገሩን ታሪክ በደማቅ ቀለም የሚጽፍበት ወርቃማ ዕድል ናት።

የሕዝብ ድምፅ የበላይ የሚሆንበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ አሸናፊ መሆኑን ለዓለም የምናሳይበት ታላቅ ቀን ናት።

ይህች ዕለት ለኢትዮጵያችን የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተማመን እና የብሩህ ተስፋ መጀመሪያ እንድትሆን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም በስኬት፣ በሰላም እና በኩራት ተጠናቅቆ ሀገራችንን ወደ ላቀ ከፍታ እንዲያሻግራት ካርድ የያዙ ዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነው።