የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅምን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝብን ወሳኝነት በተግባር ለማረጋገጥ ዝግጅት ሲደረግለት የቆየው 7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ይካሄዳል።
ይህ ታሪካዊ ምርጫ የኢትዮጵያን የነገ አቅጣጫ ከመወሰኑም በላይ የሥልጣን ምንጭ ጠመንጃ ሳይሆን በሕዝብ የነጻነት ድምፅ ብቻ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ መድረክ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአገራዊው ምርጫ አስፈላጊ የሆኑ የዝግጅት ሥራዎችን በሙሉ ማጠናቀቁን በይፋ አረጋግጧል።
ቦርዱ ባደረገው ከፍተኛ ዝግጅት መሠረት በነገው ዕለት በሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ላይ ለመሳተፍና ሉዓላዊ መብታቸውን ለመጠቀም ከ54 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መራጮች የምርጫ ካርዳቸውን ወስደው ዝግጁ ሆነዋል።
ለዚህ አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና 80 የግል ተወዳዳሪዎች የተውጣጡ 10ሺህ 934 ዕጩዎች በፉክክር ውስጥ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
ይህ የዕጩዎች ቁጥር የምርጫውን አሳታፊነትና የፖለቲካ ምህዳሩን መስፋት የሚያሳይ መሆኑ ተመልክቷል።