Search

የ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ማኅተም፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ እምቅ ኃይል

ቅዳሜ ግንቦት 22, 2018 43

ኢትዮጵያ ጥንታዊት፣ ግዙፍ እና የታሪካዊ ነፃነትና ሉዓላዊነት ተምሳሌት የሆነች ታላቅ ሀገር ዛሬም በልጆቿ ፅኑ እምነት እና ቁርጠኝነት አዲስ ብሩህ ምዕራፍ ለመጻፍ የፊታችን ሰኞ ወደ ምርጫ ኮሮጆ ታመራለች።

ይህ የታሪክ ክንውን ሀገራችን በገጠሟት ዘርፈ ብዙ የውስጥ እና የውጭ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና፣ እንዴት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታዋን በማይናወጥ መሠረት ላይ እየጣለች እንደሆነ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ግልጽ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው።

የአንድ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ቅቡልነትና ሕጋዊነት የሚለካው በሕዝቡ ተሳትፎ ስፋትና ጥልቀት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ረገድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤትነት ያለውን ፅኑ ናፍቆትና ዝግጁነት በምዝገባ ሂደቱ በተግባር አሳይቷል።

ለዚህ ታሪካዊ መነሳሳት ትልቁ ማረጋገጫ የምርጫው ቅድመ ዝግጅት በታሪካዊ የመራጮች ቍጥር የተደገፈ መሆኑ ነው፤ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የምርጫ ጣቢያዎች 54,557,861 ዜጎች የፊታችን ሰኞ ድምፃቸውን ለመስጠት በነቃ ተሳትፎና በከፍተኛ ተነሳሽነት ተመዝግበው ቀኑን እየጠበቁ ይገኛሉ።

ይህ ግዙፍ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ ሰጪ መሆኑን የማያዳግም በሆነ መንገድ ያረጋግጣል። የፊታችን ሰኞ በሚሊዮኖች ነቃ ተሳትፎ የሚዋቀረው መንግሥት፣ የሕዝብ አደራ የሚቀበል እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስከበር ሙሉ ሕጋዊ ውክልናን የሚላበስ መሆኑን ዓለም ሊገነዘበው ይገባል።

የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ግንባታ አሳታፊ፣ ብዝሃነትን ያከበረ እና ሁሉንም ያካተተ መሆኑን የሚያሳዩት ተጨባጭ ሀቆች ደግሞ ሰኞ ዕለት በሚካሄደው ውድድር የፖለቲካ ምህዳር ክፍትነት ላይ በጉልህ ይንጸባረቃሉ።

በዚህ ታሪካዊ የምርጫ መድረክ ውስጥ 42 የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የዕጩዎች ቍጥር ደግሞ 10,438 ደርሷል።

በተለይም ሥርዓቱ ከፓርቲ ፖለቲካ ማዕቀፍ ውጭም ቢሆን ለዜጎች የግል ተሳትፎ ምን ያህል ምቹና ሰፊ መሆኑን የሚያሳየው 80 የግል ዕጩዎች ቀርበው በንቃት ለመወዳደር መዘጋጀታቸው ነው።

ይህ ሀቅ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መገለል አለ ብለው ያለበቂ መረጃና በተሳሳተ ትረካ ለሚጠረጥሩ የውጭ አካላት የምህዳሩን ስፋትና እውነተኛ ውድድር የፊታችን ሰኞ በተግባር የሚያሳይ ነው።

የምርጫውን ሂደት ተአማኒነት፣ ግልጽነትና ዲፕሎማሲያዊ ከፍታ ለማረጋገጥም፣ ሀገራችን ለውጭ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት በር ሳይከፍት፣ የራሷን ተቋማዊ አቅም እና የአፍሪካዊ አጋርነትን መርህ በብልሃት ተጠቅማለች። ሀገራችን የምትደብቀው ምንም ዓይነት ምስጢር እንደሌለ በማሳየት ለግልጽነት ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠችው ሰፊ የሚዲያ ተደራሽነት እንዲኖር በማድረግ ነው፤ የፊታችን ሰኞ የሚካሄደውን ምርጫ ለመዘገብ በአጠቃላይ 68 የሚዲያ ተቋማት ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 56 የሀገር ውስጥ እና 12 ደግሞ ታዋቂ የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም፣ የምርጫው ዋና ፈራጆችና ታዛቢዎች የገዛ ዜጎቿ መሆናቸውን በፅኑ በማመን፣ 55 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሂደቱን በነፃነት እንዲታዘቡ ተዘጋጅተዋል። "ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚለው ታላቅ መርህ መሠረትም፣ የአፍሪካ ኅብረት 59 አባላት ያሉት እና ኢጋድ (IGAD) 26 አባላት ያሉት ከፍተኛ ታዛቢ ቡድኖች ምርጫውን ለመታዘብ በፍጥነት መሰማራታቸው የአህጉራዊ ተአማኒነትና የባለቤትነት ስሜታችንን ያጎላ ክስተት ነው።

የፊታችን ሰኞ ድምፅ የሚሰጥበት ይህ 54 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠበት ምርጫ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ (State-building) የሚያጠናክር ዘላቂ መሠረት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክት እጅግ ግልጽና ፅኑ ነው፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ የሚወሰነው በራሷ ሕዝብ እውነተኛ መሻትና ውሳኔ እንጂ በውጭ ኃይሎች ፍላጎት ወይም ጫና አይደለም።

ማንኛውም የኢትዮጵያን ሕዝብ ውሳኔ የሚንቅ ወይም ሂደቱን ለማዋረድ የሚሞክር እኩይ ጥረት፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፋና በፍጹም የማይቀበሉት መሆኑን በድጋሚ እናሳስባለን።

ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በዴሞክራሲያዊ መስመሯ ላይ መቼም ቢሆን አትደራደርም!