Search

ኡሁሩ ኬንያታ ለኢትዮጵያ ምርጫ ስኬት ከአፍሪካ ዲፕሎማቶች ጋር መከሩ

እሑድ ግንቦት 23, 2018 53

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በዋነኝነት ትኩረቱን ያደረገው በኢትዮጵያ ነገ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ነው።

የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ፣ ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ፕሬዝዳንት ኬንያታ 37 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 73 የአጭር ጊዜ ታዛቢዎችን ያቀፈ ጠንካራ እና ስብጥሩ የሰፋ ቡድን እየመሩ ይገኛሉ።

ይህ የታዛቢ ቡድን ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን የምርጫ ባለሙያዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና ታዋቂ የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎችን ያካተተ ሲሆን፣ የልዑካን ቡድኑ ስብጥር የአፍሪካ ኅብረት ለሥርዓተ-ፆታ ሚዛን እና ለዲሞክራሲያዊ ክትትል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ልዑኩ በመንግሥት እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተከናወኑ የመጨረሻ ዝግጅቶችን አሁን ያሉበትን ደረጃ መገምገሙ ታውቋል።

54 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጽ ለመስጠት በተመዘገቡበት በዚህ ጠቅላላ ምርጫ፣ ሂደቱ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ እድገት ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ ተወስዷል።

ይህ ለኢትዮጵያውያን የብሔራዊ ጥቅም እና የሉዓላዊነት ጉዳይ የሆነው ምርጫ፤ ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ሉዓላዊነቱን ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያሳይበት አጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ለምርጫው ሰዓታት በቀሩበት በዚህ ወቅት፣ መንግሥት የሎጂስቲክስ እና የፀጥታ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አረጋግጧል።

በኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው የታዛቢ ቡድንም የግልጽነት እና የፍትሃዊነት መርሆዎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ በመላ ኢትዮጵያ ተሰማርቶ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ይከታተላል።

የአፍሪካ ኅብረት በታዛቢዎቹ አማካኝነት በኢትዮጵያ መገኘቱ፣ አህጉሪቱ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ጉዞ ለመደገፍና ሰላማዊ እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት እንዲኖር ያላትን ጽኑ አቋም የሚያንፀባርቅ ነው።