ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከ54 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በመምረጥ ሉዐላዊነታቸውን ለዓለሙ ማህበረሰብ ያረጋግጣሉ። 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዐላዊ ጉዳይ ነው።
ይህ ታሪካዊ ዕለት የዜግነት ግዴታችንን በክብር የምንወጣበት እና የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የምንወስንበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ ወደ ኮሮጆው የሚከተው የድምፅ ካርድ፣ የሀገርን ሰላም፣ ዕድገትና የህዝቦችን አንድነት የሚገነባ ጠንካራ የመሠረት ጡብ ነው።
አባቶቻችን "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" ብለው በተረትና ምሳሌ እንዳስተማሩን፣ የ54 ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ በአንድነት ሲዋሃድ የድህነትን፣ የመከፋፈልንና የኋላቀርነትን ጠንካራ ሰንሰለት በጥሶ መጣል የሚችል የማይበገር አገራዊ አቅም ይፈጥራል።
ምርጫ የሃሳብ ልዕልና የሚረጋገጥበት የሰለጠነ መድረክ እንጂ የጥልና የልዩነት ማራዘሚያ አይደለም። የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በምርጫ ካርድ እንጂ በግጭት የማንፈታበትን ዴሞክራሲያዊ ባህል በተግባር ልናሳይ ይገባል።
ዛሬ የምንመርጠው ተወዳዳሪን ወይም የፖለቲካ ፓርቲን ብቻ ሳይሆን፣ ለልጆቻችን በኩራት የምናስረክባትን ጽኑ እና የበለፀገች ሀገር መሠረት ጭምር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ስለዚህ፣ ሁላችንም በማለዳ በነቂስ ወጥተን፣ በሰላምና በጨዋነት ድምፃችንን እንስጥ! ድምፃችን ዴሞክራሲያዊ መብታችን ብቻ ሳይሆን፣ መጻኢዋን ኢትዮጵያ የማነፅ ኃይላችን ነው።
ከምንም በላይ ሀገራችንን እናስቀድም፤ የፖለቲካ ውድድሩ ሲያበቃ ለዘለዓለም አብሮን የሚዘልቀው የማይናወጠው ኢትዮጵያዊነታችን ነውና።