Search

እውነተኛ የሕዝብ ድምፅ ኃይል

እሑድ ግንቦት 23, 2018 43

እውነተኛ የሕዝብ ኃይል የሚመነጨው ከጉልበት ወይም ከጦር መሣሪያ አፈሙዝ አይደለም፤ እውነተኛ ኃይል፣ ጥልቅ ሀገራዊ ስሜት ባዘለ እና በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ አድሮ በትንሿ የምርጫ ካርድ ላይ በሚያርፍ ውሳኔ ውስጥ ይገኛል።

ያች በሰላማዊ መንገድ ወደ ምርጫ ኮሮጆ የምትገባ አንዲት ወረቀት፣ የሕዝብን ሉዓላዊነት፣ የሀገርን ክብር እና የትውልድን አደራ ያዘለች ወደር የለሽ ታላቅ ኃይል ናት። ምርጫ ተራ የዴሞክራሲ ዐውደ ርዕይ ወይም ፖለቲካዊ ልምምድ ብቻ አይደለም።

ይልቁንም ኢትዮጵያውያን የገዛ ሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ በገዛ እጃቸው የሚወስኑበት፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውን በማያወላውል ሁኔታ ለዓለም የሚያስመሰክሩበት፣ እንዲሁም ክብራቸውን አጽንተው የሚያቆሙበት የክብር መድረክ ነው።

በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የታየው እና አሁንም እየታየ ያለው የሕዝባዊ ተነሣሽነት ማዕበል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ንቃት እና የዴሞክራሲ ጥማት ወደ አዲስ የብስለት ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው።

ከዳር እስከ ዳር፣ ከከተማ እስከ ገጠር፣ ወጣቱ እና አዛውንቱ፣ እናቶች እና አባቶች በከፍተኛ ጉጉት የምርጫ ካርዳቸውን ሲወስዱ፣ የሚያስተላልፉት አንድ ግልጽ እና ነጎድጓዳዊ መልእክት አለ - "የሀገራችን ሉዓላዊ ባለቤቶች እኛው ራሳችን ነን!" የሚል።

ይህ በመላ ሀገራችን የተስተጋባው ወደር የለሽ ተነሣሽነት ዝም ብሎ በአጋጣሚ የተፈጠረ አይደለም። ዜጎች በሀገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው፣ የሀገረ-መንግሥት ግንባታው ሂደትም ከእነሱ ይሁንታ ውጪ ሊሳካ እንደማይችል ጠንቅቀው በመረዳታቸው ነው።

በየምዝገባ ጣቢያው የታየው ረዥም ሰልፍ፣ ሁሉ ትዕግሥት፣ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር፣ ጽናት እና ብሩህ ተስፋን በጉልህ የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው። አሁን ደግሞ ይህንን አቋም በድምፅ መስጫው ዕለት ወደ ተግባር የመቀየር ታሪካዊ ኃላፊነት ከፊታችን ተደቅኗል።

የሕዝብ ድምፅ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የማይበገር የሉዓላዊነት ጋሻ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ክብር፣ ሞገስ እና ተደማጭነት፣ እንዲሁም የተለያዩ የውጭ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሟ በቀጥታ የሚመነጨው ከዚሁ ከሕዝቧ ውሳኔ ነው። በሚሊዮኖች ይሁንታና ድምፅ የተገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ከማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ የጸዳ ጠንካራ ሉዓላዊ አቅም ይኖረዋል።

ዛሬ በነቂስ ወጥተን በምንሰጠው ድምፅ፣ ለዓለም የምናስተላልፈው አንድ ኅብረ-ዜማ አለ፤ "ኢትዮጵያ የውጭ ኃይሎች መፈተኛ ወይም የጂኦ-ፖለቲካ መጠቀሚያ ሳትሆን፣ በልጆቿ የነቃ ተሳትፎ እና ፅኑ ፍላጎት ብቻ የምትመራ ሉዓላዊት እና ነጻ ሀገር ናት" የሚል ነው።

እውነተኛ የሕዝብ ኃይል ማለት፣ ሀገርን ከውስጥ በፍትሕ እና በእኩልነት ጠንካራ፣ ከውጭ ደግሞ በነፃነት የተከበረች የሚያደርግ የማይታለፍ አንጡራ አቅም ነው።

ስለሆነም፣ ይህ ታሪካዊ የምርጫ ቀን ሲያባራ ማንም ካርዱን የያዘ ኢትዮጵያዊ በቤቱ ሊቀር አይገባውም። ወንድሜ፣ እህቴ፣ አባቴ፣ እናቴ... ያንተ አንዲት ድምፅ፣ ያንቺ አንዲት ካርድ፣ የኢትዮጵያን አጽም የሚያቆም፣ የተቋማትን መሠረት የሚያጠነክር እና የነገውን ትውልድ የሰላም መንገድ የሚጠርግ የብርሃን ጮራ ነው።

ምርጫ መደበኛ የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገር ክብር የሚከፈል የጀግንነት ጥሪ፣ የነፃነት አሻራ ማሳረፊያ ነው። በምርጫ ጣቢያዎች ተሰልፈን የምንገነባው የተረጋጋ፣ ፍቅር የተሞላበት እና የሠለጠነ ሰልፍ፣ የብልጽግናችን እና የዴሞክራሲያዊ ባህላችን መሠረት ነው።

ካርዳችንን በእጃችን በክብር ይዘን፣ የወሰን አሻጋሪነት እና የውሳኔ ሰጪነት ምልክት የሆነውን ሰማያዊ ቀለም በጣታችን ላይ ስናሳርፍ፣ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እና ሉዓላዊነት እያረጋገጥን መሆኑን በሙሉ ልብ ልንገነዘብ ይገባል።

ድምፃችንን መስጠት የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ እና የልጆቻችንን መፃኢ ዕድል ለሌሎች አሳልፎ ከመስጠት ይጠብቀናል። የሕዝብ ኃይል በተግባር የሚገለጠው፣ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#EBC #Ethiopia #AUEOM #democracy See less