የባህር በር ለአንድ ሀገር የውሃ ጥም የማርካት ጥያቄ አይደለም፡፡ የብሔራዊ ክብር መገለጫ፣ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እና የስትራቴጂካዊ ነፃነት ዋስትና እንጂ። የታሪክ ማህደሮችን ገለጥ አድርገን ስንመለከት፣ ውቅያኖሶችን የተቆጣጠሩና የባህር ሀብታቸውን በአግባቡ የተጠቀሙ ሀገራት የብልጽግናን ማማ መቆናጠጥ ሲችሉ፤ በተቃራኒው በየብስ የታጠሩ ሀገራት ግን የትራንስፖርት ወጪያቸው በራሱ ብቻ ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ እየጨመረ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ሲያጡና ሉአላዊነታቸው በጎረቤቶቻቸው የፖለቲካ ፈቃድ ስር ሲወድቅ ይታያል። ይህንን የጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ሰብሮ ለመውጣት የሚደረግ ጥረት ደግሞ የዘመኑ ዋነኛ የህልውና ጥያቄ ሆኖ ተገኝቷል።
የዓለም ሀገራትን ተሞክሮ ስንቃኝ፣ የባህር በርን ለብሔራዊ ልዕልና እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አስደናቂ ትምህርቶችን እናገኛለን። በአንድ ወቅት ደካማ የነበሩት ሲንጋፖር እና ዱባይ ዛሬ የዓለም የንግድ ማዕከል ለመሆን የበቁት ጂኦግራፊያዊ መገኛቸውን ወደ ወርቅ በመቀየር ነው። ሲንጋፖር በፓስፊክ እና በህንድ ውቅያኖስ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ቦታ በመጠቀም የዓለም መርከቦች መተላለፊያ ድልድይ ስትሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ በጄበል አሊ ወደብ አማካኝነት የበረሃ መንደርነቷን ትታ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ቁንጮ ሆናለች። ኔዘርላንድስ ደግሞ በሮተርዳም ወደቧ ብቻ ሳይሆን፣ "የባህር ትውልድ" በመፍጠር ትታወቃለች፤ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ዜጎቿ ስለ ባህር ኢኮኖሚ እንዲያውቁ በማድረግ የነገውን የኢንዱስትሪ መሪ ገና ዛሬ ታዘጋጃለች።
በሌላ በኩል፣ እንደ ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት "የባህር ነፍስን" በሚል መሪ ቃል ትውልዱን በባህር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በማነቃቃታቸው ዛሬ በመርከብ ግንባታ ዓለምን የሚመሩ ግዙፍ ኃያላን ለመሆን በቅተዋል። ይህ የባህር ሉዓላዊነት ስሜት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የምንረዳው ደግሞ በቦሊቪያ ተሞክሮ ነው፤ ቦሊቪያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ያጣችውን የባህር ዳርቻ ለመመለስ ያላትን ቁርጠኝነት በየዓመቱ "የባህር ቀን" በሚል ስያሜ ስታከብርና በየብስ ላይ ሆና የባህር ኃይልን ስታሰለጥን ትውልዱ የተስፋ ስንቅ እንዲሰንቅ ታደርጋለች። ይህም የባህር በር ማግኘት ለአንድ ሀገር የሞራል እና የኩራት ምንጭ መሆኑን ያሳያል።
የየብስ እስረኝነትን በብልሃት የመስበር ጥበብ ደግሞ በስዊዘርላንድ፣ ካዛኪስታን እና ሩዋንዳ ታሪክ ውስጥ በጉልህ ይነበባል። ስዊዘርላንድ ምንም እንኳን የቀጥታ የባህር ዳርቻ ባይኖራትም፣ በዓለም ትልቁ የሆነውን የመርከብ ኩባንያ (MSC) በባለቤትነት በማስተዳደር በውቅያኖሶች ላይ የራሷን አሻራ አሳርፋለች። ካዛኪስታን እና ሩዋንዳ ደግሞ እራሳቸውን ከ"የብስ እስረኝነት" ስሜት አውጥተው "የየብስ ተገናኝ" (Land-linked) በሚል ስያሜ በደረቅ ወደቦችና በዘመናዊ ሎጂስቲክስ የቀጣናቸው የንግድ ማዕከል ለመሆን በቅተዋል። ግዙፏ ቻይናም ቢሆን የባህር ኢኮኖሚዋን ከፋይናንስ እና ከሳይንሳዊ ምርምር ጋር በማስተሳሰር የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆን የቻለችው ይህንኑ የሰማያዊ ኢኮኖሚ ስልት በመከተሏ ነው።
ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት እና በፈጣን ዕድገት ላይ ያለች ሀገር ሆና ሳለ በየብስ ታጥሮ መቆየት የልማት እንቅፋት ብቻ ሳይሆን የታሪክ እዳም ነው። በአክሱም ዘመን አዱሊስን የመሰሉ ታላላቅ ወደቦች የነበሯት ሀገር፣ ዛሬ 95 በመቶ ንግዷን በአንድ የጎረቤት ሀገር ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ማድረጓ ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ክፍያ እና ለስትራቴጂካዊ ተጋላጭነት ዳርጓታል። ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማረም የተነደፈው "የሁለት ውሃ ፖሊሲ" እና ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያን ከየብስ እስር ቤት አውጥቶ የዓለም የባህር ንግድ ተዋናይ የሚያደርጋት ስልታዊ እርምጃ ነው።
በመሆኑም፣ የባህር በር ፍለጋው የኢትዮጵያ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ እና የህልውና ጥያቄ ነው። ይህ ጥረት የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክር እንጂ ማንንም የሚጎዳ አይደለም። እንደ ስኬታማ ሀገራት ተሞክሮ ሁሉ፣ እኛም ትውልዱን በባህር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በማነቃቃት፣ የማሪታይም ዲፕሎማሲያችንን በማጠናከር እና የሰማያዊ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመተግበር ብሔራዊ ብልጽግናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ይህ የባህር በር ጥሪ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቀዳሚ ምዕራፍ እና ለነገው ትውልድ የምናስተላልፈው የታሪክ አደራ ነው።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ