Search

የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

ማክሰኞ መጋቢት 29, 2018 130

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ14ኛ መደበኛ ስብሰባው የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።
ረቂቅ አዋጁ በመንግሥት ብቻ የሚሰጠው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ ወቅቱ የሚጠይቀውን የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ሥርዓት እንዲዘረጋ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ሰብሳቢው አመላክተዋል።
በዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን የሚያማክሩ እና የመረጃ ቅብብሎሽ አገልግሎት የሚሰጡ የግል ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና የሆኑ ድርጅቶች እየታዩ በመሆኑ በግብርና ኤክስቴንሽን ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑን አቶ ሰለሞን ላሌ አያይዘው አስገንዝበዋል።
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጡ ጥራት እና ፍትሐዊነት ቁጥጥር ትኩረት የሚሻ በመሆኑ አገልግሎት የሚሰጠው በተመዘገበ እና የብቃት ማረጋገጫ ባገኘ አገልግሎት አቅራቢ መሆን እንደሚኖርበት አዋጁ የአሠራር ሥርዓት እንዳስቀመጠ ጠቁመዋል።
የግብርና ኤክስቴንሽን መሠረት ልማት ዝርጋታዎችን ማዘመን በመንግስት ላይ ብቻ በመውደቁ በሚጠበቀው ደረጃ እርካታ ያልተገኘበትን የተጠቃሚዎች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የግብርና ኤክስቴንሽን ፈንድ ለማቋቋምና ፍላጎት ለመቅረፍ ረቂቅ አዋጁ እንዳካተተ ሰብሳቢው አንስተዋል።
በግብርና ባለሙያዎች ብቻ ይሰጥ የነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሁን ላይ የምርት መጠን እና ምርታማነትን ለማሳደግ በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ ይህንን ችግር ለመፍታት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ለማሻሻልና ለማዘመን ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሀገራችን ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሠረተ መሆኑን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ በዘርፉ ምርትን በብዛት፣ በጥራት እና በቀጣይነት ለማሳደግ የግብርና ኤክስቴንሽን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ ከግብርና ምርምር የሚገኙ እና ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችን የግብርና ባለሙያው ለአርሶ አደሮች በተግባር ማሳ ላይ እያሳዩ እና እያስተማሩ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።
የምክር ቤት አባላቱ አያይዘውም የግብርና ኤክስቴንሽን ተደራሽነት ከ36% በላይ አለማለፉን ጠቁመው፣ ረቂቅ አዋጁ ይህንን ክፍተት እንደሚሞላ ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ መንግስታዊ ያልሆኑ የአገልግሎት ተዋንያን ህጋዊነትን በጠበቀ መልኩ፣ ተጠያቂነት በሰፈነበት እና ጥራቱ በጠበቀ ሁኔታ መንግሥትን እና አርሶ አደሩን በመደገፍ የግብርና ልማቱን በሚገባ እንደሚያሳልጥ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን፣ አዋጅ ቁጥር 1411/2018 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።