የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን ቀዳሚ እና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በመደመር እሳቤ የባሕር በር ጉዳይ የሀገርን ክብር ከመመለስ ባለፈ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች እና በሌሎች ላይ ጥገኛ ያልሆነች ኢትዮጵያን ለማስረከብ እንደ ቁልፍ መሣሪያ ይታያል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ ለቀጣይ ዕድገቷ ወሳኝ የሆነው የባሕር በር ሊዘጋባት አይገባም ይላሉ።
"እኛ ታፍነን እንደቆየን ልጆቻችንም ታፍነው ይቀጥሉ የሚል አካል ጤነኛ አይደለም" ሲሉም ይሞግታሉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የተነጠቀችው የሚከራከርላት አካል በመጥፋቱ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር አሸብር፣ አሁን ግን በዚህ ጉዳይ ሕዝብም መንግሥትም በአንድነት መቆማቸው ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
"ኢትዮጵያ ክብሯ ሊመለስ ይገባል፤ የባሕር በሯ ሊረጋገጥ ይገባል" የሚል ትውልድ በመነሣቱ ለውጦች እየታዩ መሆኑንም አክለዋል።
በአንዳንድ አካላት የሚነሡ ትችቶች ሚዛናዊነት የጎደላቸው መሆኑን አንጋፋው ፖለቲከኛ ያብራራሉ። "ምርጫ ለማሸነፍ ሲባል የሚነሣ ሐሳብ ነው፤ ቀደም ሲል ያልታቀደ ነው" የሚሉ አሉባልታዎች ቢሰሙም፣ መንግሥት ከለውጡ ጊዜ አንሥቶ የባሕር ኃይል ሲያዘጋጅ መቆየቱ ለጉዳዩ አስቀድሞ የተሰጠውን ትኩረት በግልጽ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ሀገራችንን የማይመጥኑ ትንንሽ ትችቶችን ትቶ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል በሚለው ላይ በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግም ዶክተር አሸብር ያስገነዝባሉ።
ዕጣ ፈንታን በሚወስነው የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ አቋም ሊይዝ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ እና ታሪካዊ ጠላቶች የሚያራምዱትን አቋም በግልጽ መቃወም እንደሚገባ የገለጹት ዶክተር አሸብር፣ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ሳይገድበን ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆም የወቅቱ አርበኝነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሲሳይ ደበበ