የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የመጀመሪያ በረራውን የጀመረበትን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ተቋሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል እና እስከ 2040 ዓ.ም የሚዘልቅ ታላቅ የዕድገት ፍኖተ ካርታ (Vision 2040) ይፋ አድርጓል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ ይህ አዲስ ራዕይ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን የአፍሪካ ቀዳሚነት ደረጃ ወደላቀ የዓለም አቀፍ ከፍታ የሚያሸጋግር ነው።
በዚሁ መሠረት እስከ 2040 ዓ.ም ድረስ አየር መንገዱ አሁን ያሉትን 145 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ወደ 203 ለማሳደግ የወሰነ ሲሆን፣ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የዘመናዊ አውሮፕላኖቹን ቁጥር አሁን ካሉበት 150 ወደ 250 እና ከዚያ በላይ ለማድረስ አቅዷል።
በአሁኑ ወቅት በዓመት 20 ሚሊዮን መንገደኞችን እያጓጓዘ የሚገኘው አየር መንገዱ፣ በ2040 ይህንን ቁጥር በሦስት እጥፍ በማሳደግ 60 ሚሊዮን ለማድረስ አልሟል።
ይህም ተቋሙ በዓመት እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ እንዲያመነጭ ያስችለዋል ተብሏል።
የአሁኑ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የታቀደውን ግዙፍ ዕድገት ለማስተናገድ በቂ ባለመሆኑ፣ በቢሾፍቱ ከተማ በመጀመሪያ ፌዝ እጅግ ዘመናዊ እና በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዲስ አውሮፕላን ማረፊያን እያስገነባ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ በረራዎች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ትራንስፖርትን ለማሳለጥ፣ አሁን ያሉትን 23 መዳረሻዎች በእጥፍ በማሳደግ 47 ለማድረስ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።
አቶ መስፍን ጣሰው በመግለጫቸው ማጠቃለያ ላይ፣ አየር መንገዱ ባለፉት 80 ዓመታት ላስመዘገበው ስኬት ለቀድሞ እና ለአሁኑ የሥራ ባልደረቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አየር መንገዱ የኢትዮጵያ የልማት፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዕድገት ምሰሶ እንዲሁም የሀገር ኩራት ሆኖ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በላሉ ኢታላ