የዓለም አቀፍ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ ውስብስብና ተለዋዋጭ እየሆነ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ከነበረችበት አጭር ተመልካች የውጭ ግንኙነት አዙሪት በመውጣት፣ ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ማዕከል ያደረገ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ገብታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከርዕዮተ ዓለም ታሳሪነት የተላቀቀና የትላንትን፣ የዛሬን እና የነገን ዓለም አቀፍ ለውጦች ያገናዘበ ‘ፕራግማቲክ’ አካሄድን የሚከተል መሆኑን በተግባር አሳይቷል ።
ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት በዚህ ዕሳቤ የተመራው ዲፕሎማሲያችን አዲስ አበባን የዓለም የፖለቲካ መሪዎች፣ የኢኮኖሚ ጠበብቶችና የዲፕሎማሲ ልዑካን የሚጎርፉባት እንዲሁም አበይት ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች የሚተላለፉባት ደማቅ የዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል፡፡
አዲስ አበባ ዛሬ ላይ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ከመሆንም አልፋ፣ የዓለም አቀፍ መሪዎችና ተቋማት ቀዳሚ መዳረሻ ሆናለች።
በ2017 ዓ.ም. ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገድ መቻሏ የዚህ ማሳያ ነው። ይህ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ስኬት አጋጣሚ ሳይሆን፣ ሀገራችን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በከተማ ልማት፣ በኮሪዶር ልማትና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ያስመዘገበችው ውጤት ማሳያ ነው።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በአንድ ኃያል ወገን ጥገኝነት ላይ ያልተመሠረተ፣ ነፃና ሚዛናዊ የሆነ አቅጣጫን ይከተላል። ይህ ሚዛናዊ አካሄድ ከምዕራቡም ሆነ ከምሥራቁ ዓለም ጋር አዳዲስ አጋርነቶችን እንድትፈጥርና ነባሮቹን እንድታጠናክር አስችሏታል። ከታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗ ለዚህ ሚዛናዊ ፖሊሲ ትልቁ ማሳያ ነው።
ከ40 በላይ ሀገራት አባል ለመሆን በጠየቁበት መድረክ ኢትዮጵያ ተመራጭ መሆኗ፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ ክብደት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህ አባልነት ለሀገራችን ሰፊ የኢንቨስትመንት ምንጭና ለምርቶቻችን ሰፊ ገበያን ከመፍጠሩም ባሻገር፣ በደቡብ-ደቡብ ትብብር (Global South) ማዕቀፍ ውስጥ ድምፃችን ከፍ ብሎ እንዲሰማ አድርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆና መመረጧ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲዋ እመርታዎች ናቸው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ፣ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አርማና የውኃ ዲፕሎማሲያችን የድል ማማ ነው። በዲፕሎማሲው መስክ፣ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በመውሰድ በሀገራችን ላይ አላስፈላጊ ጫና ለመፍጠር የተሞከረውን ሴራ፣ "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚለው የአፍሪካ ኅብረት መርህ በማምከን አሳማኝ የዲፕሎማሲ ድል ተመዝግቧል ።
ይህ ብቻም ሳይሆን፣ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓባይ ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ፣ ለዘመናት የሕግ ማዕቀፍ ያልነበረው የውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊና ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል። የሕዳሴው ግድብ ዛሬ ላይ ለአፍሪካ ራሷን የመቻል ምልክት ሆኗል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው። ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ከቀጠናው ሀገራት ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ጠንካራ ትስስር ተፈጥሯል። ኢትዮጵያ ለጂቡቲ በቀን 100 ሺህ ኩብ ሜትር ውሃ እና ከ500 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ እውነተኛ የመልካም ጉርብትና ማሳያ ሆናለች።
ዲፕሎማሲን ወደ ዘላቂ ልማት የመቀየር ስትራቴጂው ጉልህ ፍሬዎችን እያፈራ ይገኛል። በ2017 በጀት ዓመት 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ የተቻለ ሲሆን፣ የወጪ ንግዱም ወደ 8.3 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። እንደ ሳፋሪኮም እና ዳንጎቴ ያሉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ማፍሰሳቸው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ስኬቶች ናቸው። በተጨማሪም፣ ከስንዴ ዕርዳታ ጥገኝነት ወጥቶ ራስን መቻልና ምርትን ማሳደግ፣ የሉዓላዊነትና የዲፕሎማሲ አቅም መገለጫ ሆኗል።
በዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲው መስክ፣ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ዜጎች መብትና ደኅንነት እንዲከበር ሰፊ ሥራ ሠርቷል። ከተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅና የአውሮፓ ሀገራት ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነቶችን በመፈረም፣ በ2017 ዓ.ም. ለ503 ሺህ ዜጎች፣ በ2018 ዓ.ም. ደግሞ ለተጨማሪ 800 ሺህ ዜጎች ሕጋዊና ክብሩ የተጠበቀ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች በውጭ ሀገራት ችግር ውስጥ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎችን በክብር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግም ተችሏል። የዳያስፖራው ማኅበረሰብም ለሀገሩ ልማት ያለውን አስተዋጽኦ በማሳደግ፣ በ2017 ዓ.ም. 7.17 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማመንጨት ተችሏል።
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ዘርፍ እየተገበረችው ያለው ፖሊሲ፣ ብሔራዊ ክብሯን ከፍ ያደረገ፣ የዜጎቿን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላትን ተዓማኒነት ያሳደገ ነው።
አዲስ አበባ የዓለም መሪዎች መናኸሪያ መሆኗ፣ አገራችን በብሪክስ አባልነት ያገኘችው የጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም፣ የሕዳሴ ግድብ ድልና የቀጠናዊ ትስስር እርምጃዎቿ፣ ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የተጽዕኖ ፈጣሪ ኃይል ሆና መውጣቷን የሚያረጋግጡ ሕያው ምስክሮች ናቸው። ይህ የዲፕሎማሲ ልዕልና፣ ሀገራችን ከድህነትና ጥገኝነት ተላቅቃ፣ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግናና ከፍታ የምታደርገውን የማይቀለበስ ታሪካዊ ግስጋሴ ያበሥራል።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ