Search

በከፍታው የቀጠለው የኢትዮጵያ ምልክትና የአፍሪካ ኩራት

ዓርብ ሚያዝያ 02, 2018 128

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ2010 እስከ 2017 ዓ.ም ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በሁሉም ዘርፎች እጅግ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል።

የአየር መንገዱ ዓመታዊ ገቢ በሰኔ 2010 ዓ.ም ከነበረበት 2.4 ቢሊዮን ዶላር በሰኔ 2017 ዓ.ም ወደ 7.6 ቢሊዮን ዶላር በማደግ የ216.67 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።

በተመሳሳይ ወቅት አየር መንገዱ የሚያጓጉዘው ዓመታዊ የመንገደኞች ቁጥር ከ10.6 ሚሊዮን ወደ 19 ሚሊዮን በላይ ከፍ ያለ ሲሆን፣ የካርጎ ጭነት መጠንም በ95.78 በመቶ ዕድገት በማሳየት 784 ሺህ 899 ቶን ደርሷል።

የአየር መንገዱ የሰው ኃይልም በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ በሰኔ 2010 ዓ.ም ከነበረበት 16 ሺህ 241 ሠራተኞች፣ በመጋቢት 2017 ዓ.ም ወደ 28 ሺህ 889 ከፍ ብሏል።

በመሠረተ ልማት ረገድም አየር መንገዱ የአፍሪካ መግቢያ የሆነውን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች መቀበል አቅም ከ10 ሚሊዮን በታች ከነበረበት ወደ 25 ሚሊዮን በማሳደግ ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ 1 ሺህ 121 ክፍሎች ያሉት ግዙፉ ስካይላይት ሆቴል ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃ ሲሆን፤ በዘርፉ ግንባር ቀደም የሆነ እና የሀገር መሪዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ የቪአይፒ (VIP) ተርሚናልም ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

አየር መንገዱ ከ64 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም የሥራ ክፍሎች በአንድ ላይ የሚይዝ፣ ስምንት ሕንፃዎች ያሉትና በ80 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባ ዋና መሥሪያ ቤት እያጠናቀቀ ሲሆን፤ ግንባታውም በመጪው ነሐሴ ፍጻሜ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የአውሮፕላኖችን ቁጥር በማሳደግ ረገድም ባለፉት ሰባት ዓመታት ተኩል ውስጥ 74 አዳዲስ አውሮፕላኖች ወደ ሥራ ገብተዋል። ይህም በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ አውሮፕላኖችን ቁጥር 146 አድርሶታል።

በሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት የአውሮፕላን ማረፊያዎች ቁጥር ከ20 ወደ 27 ያደገ ሲሆን፣ አራት አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎችም በቅርቡ ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባ ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል እና የኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የአየር መንገዱን የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን አቅም አጎልብተዋል።

የአየር መንገዱ ስኬት በሰው ኃይል ልማትም የተደገፈ ነው። የአቪዬሽን አካዳሚውን ወደ ዩኒቨርሲቲ በማሳደግ የተማሪዎች ቅበላን ወደ 4 ሺህ ማድረስ ተችሏል።

ለሠራተኞች የሚሆን የ5 ሺህ ሰዎች የመኖሪያ ቤት እና ለበረራ ባለሙያዎች 1 ሺህ መኪኖችን መያዝ የሚችል የሕንፃ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል።

በተጨማሪም የአውሮፕላን ሞተርና ክፍሎችን የመጠገን አቅምን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ መመዝገቡን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #EthiopianAirlines #AfricanPride #AviationGrowth #Infrastructure #SuccessStory