ቻይና በአየር ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለምን የሚያስደንቅ ታላቅ እርምጃ በመውሰድ በዓለም የመጀመሪያው የሆነውንና በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ ኃይል የሚሰራ አነስተኛ የመንገደኞች አውሮፕላን የሙከራ በረራ በስኬት አከናውናለች።
ይህ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ ጥምረት ያከናወነ ሲሆን ይህም የዓለም አቀፉን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላን ሦስት ቶን የሚመዝን የመነሻ ክብደት ያለው ሲሆን እስከ 600 ኪሎ ግራም ጭነት የመሸከም ከፍተኛ አቅም አለው።
በተጨማሪም በአንድ የበረራ ጉዞ እስከ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ሲሆን ይህም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በሙከራ ላይ ካሉ በባትሪ ብቻ ከሚሰሩ መሰል አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸር ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችል ያደርገዋል።
የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ ኃይልን በአንድነት መጠቀሙ የበረራ ጊዜን ከማራዘሙ ባለፈ በከባድ ጭነትና በረጅም ርቀት ጉዞዎች ላይ የሚታየውን የኃይል እጥረት ስጋት ሙሉ በሙሉ የሚቀረፍ ይሆናል ተብሏል።
የቻይናው ፒፕልስ ዴይሊ እንደዘገበው፣ አውሮፕላኑ እንደ ሄሊኮፕተር በቀጥታ ወደ ላይ መነሳትና ማረፍ የሚችል በመሆኑ ረጅም የመንደርደሪያ ሜዳ አያስፈልገውም፤ ይህም በትልልቅ ከተሞች ውስጥ የአየር ታክሲ አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለከተማ ትራንስፖርት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ቴክኖሎጂው ለአደጋ ጊዜ እርዳታ፣ ለሕክምና አገልግሎት፣ ለቱሪዝምና ለጭነት ማጓጓዣ ተስማሚ ሲሆን የካርቦን ልቀትንና የድምጽ ብክለትን በመቀነስ የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረገ ነው።
ቻይና በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየገሰገሰች መሆኑን ያሳየው ይህ ፕሮጀክት የወደፊቱ የአየር ትራንስፖርት ይበልጥ ፈጣንና ዘመናዊ እንደሚሆን አመላካች ሆኗል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ