Search

85ኛው የዐርበኞች ድል በዓልና የዘመኑ ዐርበኝነት

ማክሰኞ ሚያዝያ 27, 2018 239

85ኛው የዐርበኞች ድል በዓል ሲታሰብ፣ ቀኑ ከድል በዓልነት ባለፈ የኢትዮጵያውያንን የማይገሰስ የነጻነት ትርጉም እና የመጪውን ዘመን የሉዓላዊነት ግብ የምንሰንቅበት የታሪክ ማኅደር ነው።

ይህ ቀን ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም ወርሮ ለአምስት ዓመታት ከቆየ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ዐርበኞች ብርቱ ተጋድሎ ድል ተመትቶ የወጣበት እና ኢትዮጵያ ለማንኛውም ወራሪ የማትበገር መሆኗን ዳግም ያስመሰከረችበት ነው።

የኢትዮጵያ ዐርበኞች ተጋድሎን ልዩ የሚያደርገው፣ በወቅቱ የነበረው ማዕከላዊ መንግሥት መዋቅር ፈርሶ መሪው በስደት ላይ ቢሆኑም፣ የነጻነት ትግሉ ግን ሳይቋረጥ ሕዝባዊ በሆነ እና ባልተማከለ መልኩ መቀጠሉ ነው።

"መሪ አልባ" ይመስል የነበረው ተጋድሎ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለነጻነቱ ያለውን ቀናዒነት በተግባር ያሳየበት ነው።

እንደ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ እና ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) ያሉ ዐርበኞች በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ያካሄዱት የሽምቅ ውጊያ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በሕዝብ ልብ ውስጥ ጭምር እንጂ በቢሮክራሲያዊ መዋቅር ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዳልሆነ አሳይቷል።

ለኢትዮጵያውያን፣ "ነጻነት" የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ከባዕድ ኃይሎች የሚሰጥ ስጦታ ሳይሆን፣ ከፈጣሪ የተቸረ እና በታሪክ ሂደት ውስጥ የጸና የማይገሰስ መብት ተደርጎ ይወሰዳል።

ዐርበኞቻችን መተኪያ የሌላትን ሕይወታቸውን የገበሩትና ዱር ቤቴ ብለው የተንከራተቱት የነጻነትን ጣፋጭ ስሜት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።

እነ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ በግዞት ከነበሩበት እስር ቤት አምልጠው በባዕድ ሀገር የጠላትን አንገት ያስደፉትና ያን ሁሉ አስደናቂ ጀብዱ የሠሩት፣ እነ ሌተና ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ገና በለጋ የልጅነት ዕድሜያቸው ጫካ በመውረድ ፋሽስትን አርበድብደው የነጻነትን ዋጋ ያሳዩት፣ እነ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ እና ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ በስተርጅና ዕድሜያቸው "አቅም ያጥረናል" ሳይሉ እንደ ወጣት አንበሳ ጠላትን ፊት ለፊት የተጋፈጡት ለዚህ ነጻነት ነበር።

እንደ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ያሉ ሴት ዐርበኞቻችንም ተፈጥሮ ሳይገድባቸው፣ ብርዱንና ሙቀቱን፣ ርሃብና ጥማቱን ታግሰው በዱር በገደሉ የተንከራተቱት፣ የነጻነትን ጣፋጭ ስሜት ለማጣጣም ነው።

ይህ የነጻነት ትርጉም በዐርበኞቹ ዘንድ የነበረው ቦታ እጅግ የላቀ በመሆኑ፣ የካቲት 1929 ዓ.ም በተፈጸመው የግራዚያኒ ጭፍጨፋ በሕዝቡ ላይ ሽብርን ለመፍጠር ቢታሰብም፣ ውጤቱ ግን በተቃራኒው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ወደ ዐርበኝነት ቀይሯል።

ኢትዮጵያውን ለነጻነታቸው የሚሰጡት ቦታ በማንኛውም ሁኔታ ለድርድር እንደማይቀርብ እነ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ምስክር ናቸው።

የዛሬው ትውልድ ይህን የድል በዓል ሲያከብር፣ የቀድሞ አባቶቻችን በደማቸው ነጻ ኢትዮጵያን እንዳስረከቡን ሳይዘነጋ፣ የዘመኑን ዐርበኝነት በመላበስ መሆን አለበት።

የዘመኑ ዐርበኝነት ደግሞ ድህነትንና ኋላቀርነትን አሸንፎ የተሟላ ሉዓላዊነት ያላትን ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል።

የተሟላ ሉዓላዊነት የዳር ድንበር መከበር ብቻ ሳይሆን፣ በምግብ ራስን መቻል፣ በኢንዱስትሪ ማደግ እና በቴክኖሎጂ መራመድ መሆኑን የዘመኑ ምሁራንና መሪዎች ያሳስባሉ።

ልክ እንደ ትናንትናዎቹ ዐርበኞች ሁሉ፣ ዛሬም በልማት፣ በሰላምና በብልጽግና መስክ የሚሰማራው ዜጋ ሁሉ የሀገሩን ክብር የሚያስጠብቅ ዓርበኛ ነው።

የዐርበኞች ድል ቀን የትናንትናውን ጽናት ለዛሬው ልማት የምንጠቀምበት የብርታት ምንጫችን ነው።

የቀድሞ አባቶቻችን ለነጻነት የነበራቸው ቀናዒነት ዛሬ ደግሞ ድህነትን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል ውስጥ ሊደገም ይገባል።

ድህነት የሰው እጅ ያሳያል፤ የሌሎች ባሪያ ያደርጋል፤ ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ ያደርጋል፤ ስለ ራሳችን ጉዳይ በራሳችን እንዳንወስን ያደርገናል፤ ከሰው በታች ያደርጋል፤ ያስንቃል።

እናም ይህን ጠላት በጋራ ዘምተን ማጥፋት እና ነጻነታችንን የተሟላ ማድረግ የዘመናችን ታላቁ ዐርበኝነት ነው።

ይህ ታሪካዊ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን፣ ትውልዱ የዐርበኞቹን አደራ በመጠበቅ ጠንካራና በራሷ የምትተማመን ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።

በለሚ ታደሰ

#Ethiopia #patriotism #freedom #sovereignty #development #EBC