Search

የኢትዮጵያ አዲስ የተቋማዊ ግንባታ ጉዞ

ሓሙስ ሚያዝያ 29, 2018 43

በአንድ ሀገር የታሪክ ጉዞ ውስጥ መንግሥታት ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፡፡ መሪዎች ይፈራረቃሉ፤ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምም ይቀያየራል፡፡ ነገር ግን ሀገርን አፅንተው የሚያቆሙት፣ የዜጎችን መብትና ደህንነት አስከብረው የሚያሻግሩት ተቋማት ናቸው።

ኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት በፍትሕ፣ በዲሞክራሲና በኢኮኖሚ መስኮች የገጠሟት ፈተናዎች ምንጫቸው የባለሙያ እጥረት ሳይሆን የተቋማት መላላትና የወገንተኝነት ደዌ ነበር። ዛሬ የምናየው የተቋማት ግንባታ ሂደት ይህንን የታሪክ ስብራት ለመጠገንና ለነገዋ ኢትዮጵያ የማይናወጥ መሠረት ለመጣል የሚደረግ ትንቅንቅ ነው።

ትላንት፡ ተቋማት እንደ ፖለቲካ መሣሪያ

ከስምንት ዓመታት በፊት የነበረውን የተቋማት ቁመና ስንቃኝ፣ የሕዝብ መጠጊያ ከመሆን ይልቅ የጥቂቶች መጠበቂያ ሆነው መቆየታቸው ግልጽ ነው። በተለይም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የነበረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። "ሕግ ለጥቂቶች መጠበቂያ፣ ለብዙኃኑ ደግሞ ማጥቂያ መሣሪያ" በሆነበት ሥርዓት ውስጥ ማኅበራዊ ውል (Social Contract) መላላቱ አይቀሬ ነበር።

የፍትሕ ተቋማት ከሙያዊ ብቃት ይልቅ ለፖለቲካ ታማኝነት ቅድሚያ እንዲሰጡ መደረጉ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህ ሁኔታ ዜጎችን ለስደትና ለእስራት ከመዳረጉም ባለፈ፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን እምነት ሸርሽሯል። የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት ተቋማት ሲዳከሙ ብሔርተኝነትና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች እንደ አማራጭ መጠጊያ ይፈጠራሉ። በኢትዮጵያም የታየው ይኸው ነበር፤ ዜጎች ከመንግሥታዊ ጥበቃ ይልቅ ወደ ብሔር አደረጃጀታቸው እንዲጠጉ በማድረግ የጋራ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲላላ ሆኗል።

የዲሞክራሲያዊ ተቋማት መታፈን

እንደ ምርጫ ቦርድ እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያሉ ተቋማት በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ኢትዮጵያ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን እንደ ብርቅ እንድትመኝ አድርጓታል። የሕዝብ ድምፅ ዋጋ በሚያጣበትና የሐሳብ ልዩነቶች በውይይት ከመፈታት ይልቅ በኃይል በሚታፈኑበት ሁኔታ የቂምና የበቀል ክምችት መፈጠሩ አልቀረም።

ዲሞክራሲያዊ ተቋማት የአንድ ሀገር የደኅንነት የደም ስሮች ናቸው። እነዚህ የደም ስሮች ሲዘጉ የፖለቲካ ውጥረት ይገነፍላል፤ ይህም ለሀገር ህልውና አስጊ የሆኑ ግጭቶችን ይወልዳል። ባለፉት አሥርት ዓመታት የታዩት ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችም የዚሁ ተቋማዊ ድክመት ውጤቶች ነበሩ።

የኢኮኖሚ ተቋማትና ተጠያቂነት

በኢኮኖሚው መስክ ገለልተኛ የቁጥጥር ተቋማት አቅም በማጣታቸው፣ የሀገር ሀብት በጥቂት ግለሰቦች እጅ እንዲከማች መንገድ ከፍቷል። ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ያለ በቂ ቁጥጥርና ተጠያቂነት ለብክነት መዳረጋቸው የሀገርን ጥሪት ለግል ጥቅም እንዲውል ሲያደርግ ቆይቷል። ተቋማት ወገንተኝነት ሲያሳዩ ገበያው ነጻ ከመሆን ይልቅ በሞኖፖልና በጥቅም ትስስር (Cronyism) ይተበተባል።

አዲሱ ምዕራፍ፡ የተቋማት ግንባታ በመደመር እሳቤ

የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ትኩረቱን በፈረሱ መሠረቶች ላይ አዲስ ግንባታ ማካሄድ ላይ ማድረጉ ይታወቃል። "ሀገር አስቀጣይ ተቋማት" የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ሥርዓት ሲቀየር የማይናወጡ፣ ግለሰቦች ሲሄዱ የማይከስሙ እና የሕዝብን አደራ በአግባቡ የሚሸከሙ ተቋማትን ይገልጻል። ይህንን እውን ለማድረግ በለውጡ መንግሥት የተወሰዱ ተጨባጭ ርምጃዎች በርካታ ናቸው።

የጸጥታና ደኅንነት ሪፎርም ተቋማቱ ከአንድ ቡድን ዕድሜ ማራዘሚያነት ወጥተው ለሕግና ለሀገር ሉዓላዊነት ብቻ እንዲቆሙ አስችሏል። ተቋማቱ በቴክኖሎጂ እንዲዘምኑና በሥልጠና እንዲዳብሩ መደረጉ የሀገርን ተፈሪነት ያረጋግጣል። በሌላ በኩል የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋም ኢትዮጵያ ከዘመኑ ጋር አብራ ለመራመድ ያላትን ዝግጁነት ያሳያል። ቀደም ሲል በኪሳራ ውስጥ የነበሩ ድርጅቶችን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር በማጣመር ለትርፍ እንዲበቁ ማድረግ መቻሉ የተቋማዊ አስተዳደር (Corporate Governance) ውጤት ነው።

ተቋማዊ ግንባታ እንደ ብሔራዊ ህልውና ዋስትና

የኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ምንጭ ከጸጥታ ተቋማት ድክመት ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ዕሴቶች ጉድለት የሚመጣ ጭምር ነው። ይህንን ለመሻገር ተቋማቱ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራና ምርምር ምንጭ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። ዜጎች በተቋማቱ ላይ እምነት ሲኖራቸውና ተቋማቱም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ሕዝብን ሲያገለግሉ የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን ይሆናል።

የተጀመረው የተቋማት ሪፎርም በየዘርፉና በየደረጃው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማትን ማብዛት የሀገረ መንግሥት ግንባታ (State Building) ሥራው ዋና ምሰሶ ነው። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ሊጸና የሚችለው ከመንግሥት መለዋወጥ ጋር የማይፈርሱ ነጻና ሕዝባዊ ተቋማት ሲፈጠሩ ብቻ ነው። እነዚህ ተቋማት የሀገራችን የጀርባ አጥንት ናቸው፤ እነሱ ሲጠነክሩ ኢትዮጵያ ትቆማለች። ስለሆነም ተቋማዊ ሪፎርሙ የፖለቲካ ምርጫ ሳይሆን የህልውና ግዴታ ነው።

በረከት ሽመልስ