የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ በኩታ ገጠም ወይም በክላስተር እርሻ ላይ የሚታዩ የአስተሳሰብ ድንበሮችን ማፍረስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን ሸዋ ዞን የስንዴ ልማት የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አርሶ አደሮች በእሳቤ የፈጠሩትን ድንበር አፍርሰው መሬቱን በማገናኘት ማረስ ከቻሉ ታላቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ይህ የተበታተነ መሬትን በማቀናጀት ወጥ የሆነ ምርት የማምረት ሂደት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል በአመራር ድክመት ምክንያት የግብርናው ዘርፍ ውጤት ዝቅተኛ ሆኖ ቢቆይም፣ አሁን ላይ በየዓመቱ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አስደማሚ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም ካደገ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ 500 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ እንደሚቻልና ለዚህም የአርሶ አደሩ፣ የባለሙያዎችና የአመራሩ ሚና ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለይም አመራሩ የዝናብ ወራትን በብቃት ለመጠቀምና ዝናብን ለማቆር የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን መፍጠር እንዳለበት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ እንዳላትና በመንግሥት እየተደረገ ያለው እገዛ አዋጭ መሆኑ በተግባር መረጋገጡን አብራርተዋል።
"ካረስን፣ የጀመርነውን ከጨረስን እና ከበረታን ችግሮቻችንን እንሻገራለን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሥራ ውጭ ሌላ የመሻገሪያ መንገድ እንደሌለ በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ ጊዜውን በሥራ እና በልማት እንዲያሳልፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ