Search

ከመሸመት ወደ ማምረት፡ የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ስኬቶች

ሓሙስ ሚያዝያ 29, 2018 60

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢኮኖሚ መዋቅሯን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ግዙፍና ታሪካዊ እርምጃዎችን እየወሰደች  ትገኛለች። ይህ የሽግግር ጉዞ የሀገራችንን የብልጽግና ራዕይ ከማሳካት ባለፈ፣ ዘላቂ የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና ራስን ለመቻል እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተወስዷል።

መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረትና ተግባራዊ የተደረጉት አዳዲስ ፖሊሲዎች፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ከነበረበት የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ወጥቶ ወደ ተሻለ የማምረት አቅም እንዲሸጋገር ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። 2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ የዘርፉ ዓመታዊ ዕድገት ቀደም ሲል ከነበረበት 4.8 በመቶ በአሁኑ ወቅት ወደ 10.7 በመቶ በመመንጠቅ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል። 

የመንግሥት ስትራቴጂካዊ ትኩረትና ኢትዮጵያ ታምርትንቅናቄ ፋይዳ

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት የወሰዳቸው እርምጃዎች ጥልቅ በሆኑ መዋቅራዊ ሪፎርሞች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። 2014 .. በይፋ የተጀመረውኢትዮጵያ ታምርትንቅናቄ፣ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ተጋርጠው የነበሩ መዋቅራዊና ፖሊሲያዊ ማነቆዎችን በመፍታት ኢኮኖሚውን ከመሸመት ወደ ማምረት ለማሸጋገር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ይህ ንቅናቄ በተለይም ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ዳግም ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ ታላቅ ስኬት አስመዝግቧል። በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 993 ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ምርት ተመልሰዋል። 3 ሺህ 680 አዳዲስ ባለሀብቶች ደግሞ ወደ አምራች ዘርፉ እንዲገቡ ተደርጓል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል የሆነው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ፣ በዋናነት የግል ባለሀብቱን ሚና ማጎልበትና አምራች ዘርፉን ከውጭ ጥገኝነት ማላቀቅ ላይ ያተኩራል። ከዚህ ጎን ለጎን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተገነቡት የተቀናጁ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ምርትን በማቀነባበር እና እሴት በመጨመር የኢንዱስትሪውን ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፉት ይገኛሉ።

በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት እንደሚያሳዩት፤ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርቡ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቶች ላይ የታዩት መሻሻሎች ለዘርፉ ማገገም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህም ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የያዘችው ግብ ከግምት በላይ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል። 

የምርት አቅም ዕድገትና የገቢ ምርቶች ተኪነት

2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የተመዘገበው ሌላው ትልቅ ስኬት፣ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ መጠናከሩ ነው። ቀደም ሲል 46 በመቶ ብቻ የነበረው የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 66.3 በመቶ ማደጉ 'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ ዐቢይ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህም በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ ብቻ 4.85 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል። በዚህም የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻ 30 በመቶ ወደ 44 በመቶ ከፍ ብሏል። በተለይም ወታደራዊ አልባሳት እና የቢራ ብቅልን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል። 

የውጭ ምንዛሬ ግኝትና የሥራ ዕድል ፈጠራ

የኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግና የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ 433 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።

ዘርፉ በትክክለኛው መስመር ላይ በመሆኑም፣ የአምራች ኢንዱስትሪው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራ ድርሻ ወደ 15 በመቶ ከፍ ብሏል። በተጨማሪም መንግሥት እና የግል ዘርፉ በፈጠሩት ጤናማ ውይይትና የፐብሊክ-ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ (PPP) ሥርዓት፣ ዜጎች በስፋት ተጠቃሚ የሚሆኑበት የሥራ ባህል ተገንብቷል። ይህም የማኅበራዊ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በቀጣይነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው። ይህ ውጤት የተገኘው የምርት ጥራትን በማሻሻልና አዳዲስ ገበያዎችን በመፈለግ ረገድ በተከናወኑ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና የንግድ ሥርዓት ማሻሻያ ሥራዎች ነው።

ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች

በዘርፉ የላቁ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ አሁንም አንዳንድ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይካድም። የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የግብዓት ትስስር ማነስ፣ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ፣ እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት ማነስ አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።

ይሁን እንጂ መንግሥትና የግል ባለሀብቱ ኢትዮጵያ ታምርትንቅናቄ አማካኝነት የጀመሩት የተቀናጀ የሥራ ባህል እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ አቅም ፈጥሯል።

ወደፊትም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን፣ አረንጓዴ የኢንዱስትሪ ልማትን በመተግበር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በማስቀረትና የኤክስፖርት ገቢን በማሳደግ፤ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ራዕይ ከምንጊዜውም በላይ እውን ለመሆን ተቃርቧል።

በለሚ ታደሰ