Search

የዘመኑ ታላቁ ዐርበኝነት - የባሕር በራችንን ማስመለስ

ማክሰኞ ሚያዝያ 27, 2018 255

ዛሬ የጀግኖች ዐርበኞች ቀንን ስናከብር፣ የአባቶቻችንን ገድል የምናወሳው በታሪክ ማኅደር ውስጥ ለተቀመጠ ትዝታ ብቻ አይደለም።

ይልቁንም ያ በደም እና በአጥንት የተገነባው የሀገር ሉዓላዊነት እና የነፃነት መንፈስ ዛሬ ላለብን ትውልዳዊ ኃላፊነት ስንቅ እንዲሆነን ጭምር ነው።

ዐርበኞቻችን መሥዋዕትነት የከፈሉት ሀገርን ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ክብርን እና የቀጣይ ትውልድ ዕድልን ለማስቀጠል ነበር።

ሆኖም፣ ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት በሴራ እና በአሻጥር የደረሰብን ‘ስትራቴጂያዊ ስብራት’ ሀገራችንን የባሕር በር አልባ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባትን ተፅዕኖ እንዳታሳርፍ እና "በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት" እንድትቆይ አድርጓታል።

የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ወይም ተራ የፖሊሲ ጉዳይ ሳይሆን፣ የሀገርን ሕልውና የማስቀጠል ጉዳይ ነው።

ዛሬ የምናከብረው እውነተኛው ዐርበኝነት፣ ይህን የታሪክ ስህተት በማረም የኢትዮጵያን የባሕር በር ሉዓላዊነት የሚያረጋገጠውን ነው።

ታላላቅ አባቶቻችን ሀገርን ለማቆየት ግንባር ለግንባር ተጋፍጠው ደማቸውን እንዳፈሰሱት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ሀገራችን በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ከ2 ቢሊዮን በላይ ዶላር በማስቀረት እና ይህን ሀብት ለልማት በማዋል የኢኮኖሚ ዐርበኝነቱን ሊያሳይ ይገባል።

ይህ ወጪ በየሦስት ዓመቱ አንድ ተጨማሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መገንባት የሚያስችል አቅም እንደሆነ መረዳት፣ የወደብ ጉዳይ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ያሳያል።

ኢትዮጵያ እንደ ዓለማችን በሕዝብ ብዛት ቀዳሚዋ ሀገር ዝግ ሆና መቀጠሏ፣ በየዓመቱ ከ13% እስከ 23% የሚደርስ የGDP ዕድገቷን እንድታጣ አድርጓታል።

ይህ ማለት በዜጎች ኑሮ ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት፣ የሥራ አጥነት እና የድህነት ጫና በቀጥታ ከባሕር በር እጦት ጋር የተቆራኘ ነው።

ስለሆነም፣ የአሁኑ ትውልድ በዲፕሎማሲ፣ በሕግ እና በስትራቴጂያዊ ጥበብ የባሕር በርን ዳግም ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት የዘመኑ "ታላቁ ዐርበኝነት" ነው።

የባሕር በር ማግኘት ማለት የኢኮኖሚ ነፃነትን ማወጅ፣ በቀጣናው የሚገባንን ሥልጣን እና ተፅዕኖ መመለስ፣ እንዲሁም ለሚሊዮኖች ዜጎች የተሻለ ኑሮን ማረጋገጥ ማለት ነው።

አባቶቻችን በጀግንነት በመፋለም በሰይፍ እና በጎራዴ ሀገርን እንዳቆዩልን ሁሉ፣ እኛም የእነርሱን ገድል የሚያስቀጥል፣ ሀገር የሚያኮራ ተግባር የምንፈጽመው፣ ኢትዮጵያን ከገባችበት መልክዓ-ምድራዊ እሥር በማላቀቅ እና ሉዓላዊ የባሕር በር ባለቤት በማድረግ የወደፊት ዕድሏን ብሩህ ስናደርግ ብቻ ነው።

ይህ የዘመኑ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ተረክቦ፣ በጽናት እና በብልሃት የባሕር በሯን በማስከበር ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሣኤ የሚነሣበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

#EBC #Ethiopia #patriotism #seaaccess