ኢትዮጵያ የሕክምና ምርቶች ማምረቻ ዘርፍን ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ እንደ ሀገራዊ የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመቁጠር ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች። በተለይም በቅርቡ በአዲስ መልክ ተስፋፍቶ የተመረቀው የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (AHRI) ፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ አህጉር አዲስ የሳይንስ ዘመን ጅማሮን ያበሰረ ክስተት ሆኗል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢንስቲትዩቱን አቅም ማሳደግ እንደ አንድ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን፣ የ"መድኃኒት ሉዓላዊነት" መሠረታዊ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል። የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ እሳቤ ማንኛዋም ሀገር የዜጎቿን መሠረታዊ የጤና፣ የምግብ እና የኢንዱስትሪ ፍላጎቶች ማሟላት ካልቻለች እውነተኛ ሀገራዊ ነፃነት ሊኖራት አይችልም የሚል ነው፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፖሊሲ ለውጥ መነሻ
ለዚህ ስትራቴጂያዊ የዘርፍ ሽግግር ዋነኛ መነሻ የሆነው፣ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ያስተማረው መራራ ትምህርት ነው። ቀውሱ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አቅጣጫ ያስቀየረ ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ሆኖ አልፏል። ከወረርሽኙ በፊት ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የመድኃኒት ፍላጎቷን ከውጭ ገበያ ታስገባ የነበረ ሲሆን የሀገር ውስጥ አምራቾች ይሸፍኑ የነበረው ከ8 በመቶ የማይበልጥ ድርሻን ነበር።
ይህ ከፍተኛ ጥገኝነት ኢትዮጵያን ለአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና ለፍትሐዊ ያልሆነ የዓለም አቀፍ የክትባት ስርጭት አጋልጧት ቆይቷል። ሆኖም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች እንደሚያሳዩት፤ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፍ ጭምር የነበረባትን ጥገኝነት በመቀነስ፣ 9 ክልሎች የራሳቸውን ፍላጎት በራሳቸው እንዲሸፍኑ ማድረግ ችላለች። ይህም የ"መድኃኒት ሉዓላዊነት" ጉዞው በተጨባጭ ውጤት የታገዘ መሆኑን የሚያረጋግጥ ትልቅ ማሳያ ነው።
የማምረት አቅም ግንባታ እና የቀጣይ ዕድገት አቅጣጫ
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የክትባት አቅርቦት ላይ የታየውን ክፍተት ለመድፈን መንግሥት የክትባት ምርትን በሀገር ውስጥ ለማስጀመር ልዩ ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ብሔራዊ የክትባት ማምረቻ አቅሟን ለመገንባት እና መሰረታዊ የሆኑ ክትባቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የ"ShieldVax Enterprise" ፕሮጀክትን ጨምሮ ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡ የሀገራችን የክትባት ምርት ዕቅድ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተዘጋጁ ክትባቶችን በማምጣት በመሙላት እና በማሸግ (Fill and Finish) ሂደት የሚጀመር ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከጥሬ ዕቃ ጀምሮ በሀገር ውስጥ የማምረት (End-to-End manufacturing) ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተነድፎለት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይህም ሀገራችንን ከውጭ ጥገኝነት በማላቀቅ ለቀጣናው የክትባት አቅርቦት ማዕከል እንድትሆን ያስችላታል።
ወቅታዊ አፈጻጸም እና የማኑፋክቸሪንግ ዕድገት
በዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱ መሠረት፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው የተኪ ምርት ድርሻ 58 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል። ይህ አጠቃላይ ስኬት የመድኃኒት ምርት አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚደግፍ ነው። በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት ብሔራዊ ፍላጎቱን 44 በመቶ መሸፈን የቻለ ሲሆን፣ ይህንን አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ 55 በመቶ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል።
መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ራስን የመቻል አቅም ላይ እንዲደርስ ስትራቴጂካዊ ግብ አስቀምጧል። ከአሁኑ የ44 በመቶ አፈጻጸም ተነስቶ በአምስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ዕቅድ፣ ደፋር ቢመስልም በተደራጀ መንገድ የተቀመጠ ተግባራዊ ግብ ነው። እስካሁን ከተመዘገቡት ስኬቶች አኳያ፣ ይህ መቶ በመቶ ራስን የመቻል ራዕይ እንደሚሳካ አያጠራጥርም።
በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የታየው ፈጣን ዕድገት፤ ሀገራችን በኬሚካል እና በሕክምና ግብዓቶች ራስን ለመቻል የጀመረችው ጉዞ በተጨባጭ ውጤት እየታገዘ መሆኑን ያረጋግጣል።
የአርማወር ሐንሰን (AHRI) ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ሚና
የኢትዮጵያን የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ግብ ለማሳካት የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እንደ ቴክኒካዊ የጀርባ አጥንት ያገለግላል። አዲሱ ማዕከል 40 የላቁ ላቦራቶሪዎችን እና ዘመናዊ የባዮኢኩቫለንስ (Bioequivalence) ማዕከልን የያዘ ነው። ቀደም ሲል አምራቾች ናሙናዎችን ለምርመራ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ ይገደዱ ነበር፤ ይህም በምርት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ወጪን፣ መዘግየትን እና የውጭ ምንዛሬ ብክነትን ያስከትል ነበር። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከምርምርና ሙከራ ጀምሮ እስከ ማረጋገጫ መስጠት ያለውን ሂደት በሀገር ውስጥ በማከናወን ይህንን የውጭ ጥገኝነት እያስቀረች ትገኛለች።
በተለይም የባዮኢኩቫለንስ ማዕከሉ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ጄነሪክ (Generic) መድኃኒቶች፣ ከዋናው ብራንድ መድኃኒት ጋር ተመሳሳይ የፈውስ አቅምና ደኅንነት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥበት በመሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ መሠረተ ልማት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂው መሠረት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ የምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረጉ፣ የመድኃኒት ግኝት ሂደቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ ያስችለዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በመድኃኒት ምርት ራስን ለመቻል የያዘችው የ5 ዓመት ዕቅድ፣ አሁን ካለው የ58 በመቶ የተኪ ምርት አፈጻጸም እና በሳይንሳዊ ምርምር ማዕከላት ግንባታ ረገድ ከተመዘገቡት ስኬቶች አንጻር ሲታይ፣ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘው ግብ በትክክለኛው ጎዳና ላይ መሆኑን ያረጋግጣል።
በለሚ ታደሰ