ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ያላት ስትራቴጂካዊ መገኛና የተፈጥሮ ጸጋዎቿ የብልፅግናዋ መሰረት ብቻ ሳይሆኑ የህልውናዋም ምሶሶዎች ናቸው።
ይህች ጥንታዊት ሀገር በቀይ ባሕር ዳርቻ የተፈጠረችና የታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ እንደመሆኗ፣ የኢኮኖሚና የደህንነት ትልሟ ከእነዚህ ሁለት ታላላቅ የውኃ አካላት ጋር በእትብት የተቆራኘ ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን ከእነዚህ የተፈጥሮ በረከቶቿ ለመነጠል በባዕዳንና በውስጥ ባንዳዎች የተሸረቡ ሴራዎች ኢትዮጵያን "የመልክዓ-ምድር እስረኛ" አድርገው አቆይተዋታል።
ከሰላሳ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ከ90 በመቶ በላይ የሚከናወነው በራሷ የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦች በኩል የነበረ ቢሆንም፣ በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ የተፈጸሙ የታሪክና የፖለቲካ ስህተቶች ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር እንድትቀር አድርገዋታል።
በተለይም በወቅቱ የነበረው አመራር "ወደብ ሸቀጥ ነው" በሚል የጠበበና የሀገርን ሉዓላዊ ጥቅም ለድርድር ያቀረበ አመለካከት በመያዙ፣ ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ መዋዠቅና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንድትጋለጥ አድርጓታል።
ይህ የጂኦ-ፖለቲካዊ እስረኛነት ኢትዮጵያን በአንድ የወደብ መስመር ላይ ብቻ ጥገኛ በማድረግ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የኢኮኖሚዋን እድገት እየገታው ይገኛል። ዛሬ ግን የለውጡ መንግስት ይህንን የታሪክ ስብራት ለመጠገንና የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት አጀንዳ ከአፈርና ከአቧራ አራግፎ ወደ ዓለም አቀፍ አደባባይ አውጥቶታል።
የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ወይም የአምባገነንነት ፍላጎት ሳይሆን የ130 ሚሊዮን ህዝብ የህልውና እና የክብር ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን "የጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጥገኝነት" ለመስበር ቆርጣ የተነሳች ሲሆን፣ ጥያቄውም በሌሎች ሀገራት ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ (UNCLOS) እና ታሪካዊ መብቶች ላይ የተመሰረተ ተፈጥሯዊ መብትን የማስከበር ሂደት ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የባሕር በር ጥያቄን በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ አድርጋ በማንሳት ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በስፋት እያከናወነች ትገኛለች። ይህም ቀደም ሲል "የማይነካ" ተደርጎ ይወሰድ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር፣ ዜጎች ስለ ሀገራዊ ጥቅማቸው በነጻነትና በኩራት እንዲወያዩ ዕድል ፈጥሯል። ከአንድ ወደብ ጥገኝነት ለመውጣትም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ትሥሥር በመፍጠር አማራጭ ወደቦችን የማስፋፋት ስራዎች ተጀምረዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር ጥቅም ለማስጠበቅ የሚችል ዘመናዊና ጠንካራ የባሕር ኃይል መልሶ የማደራጀት ተግባርም የዚሁ ታላቅ እቅድ አካል ነው። ወደፊትም ኢትዮጵያን ከጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጥገኝነት ወደ ተረጋጋ ቁመና ለማሻገር፤ ሰላማዊና ህጋዊ ድርድሮችን ወደ ተጨባጭ ስምምነት የማሸጋገር ስራ በትኩረት ይከናወናል።
የመንግሥት መርህ የሰጥቶ መቀበል ፍልስፍና እንጂ የጥቃት ወይም የጦርነት መንገድ አይደለም። በቀይ ባሕር አካባቢ የሚከሰቱ የጸጥታ ስጋቶችና የጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች የኢትዮጵያን የንግድ ፍሰት እንዳያስተጓጉሉ፣ ከቀጠናው ሀገራት ጋር በጋራ የደህንነትና የልማት ማዕቀፎች ላይ መስራት የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ከታሪክ አኳያ ፍጹም ተገቢነት ያለው ነው። ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውኃ አካል የሆነውን የዓባይን ተጠቃሚነት በታላቁ የህዳሴ ግድብ በኩል በክንዷና በልጆቿ ጥረት እንዳረጋገጠች ሁሉ፣ ሁለተኛው የውኃ በረከት የሆነው የባሕር በር ባለቤትነትም የማይቀለበስ የትውልድ ጥያቄ ነው። የባሕር በር ከሸቀጥ ልውውጥ ባለፈ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከኤዥያና ከአውሮፓ ጋር የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወሳኝ ድልድይ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሺህ ዓመታት የታሪክ ጉዞዋ የቀይ ባሕር ንግስትና የሰላም ዘበኛ ሆና መቆየቷ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይሁን እንጂ በቅርብ የታሪክ አጋጣሚዎች የገጠሟት ፈተናዎች ለዘመናት የገነባችውን የባሕር ኃይልና የወደብ ሐብት እንድታጣ አድርገዋታል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የፍጆታና የኢንዱስትሪ ዕቃዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህንን እድገት የሚሸከም አስተማማኝ ወደብ አለመኖሩ ደግሞ የንግድ ሥርአቱን ለውጭ ኃይሎች ጫና ተጋላጭ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ በየቀኑ ለወደብ አገልግሎት የምትከፍለው ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ገንዘብ ለሀገራችን የልማት ፕሮጀክቶች መዋል የሚችል ትልቅ ሀብት ነው። ይህንን ኪሳራ ለማስቀረት የባሕር በር ባለቤትነት አማራጭ የሌለው ብሔራዊ ግብ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ፍትሃዊና አብሮ ለማደግ የታለመ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ አስረድታለች። "የሰጥቶ መቀበል" መርህ ኢትዮጵያ የባሕር በር ስታገኝ ለጎረቤቶቿ ደግሞ በኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት የምታበረክተውን ትልቅ ድርሻ የሚያመለክት ነው።
ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ወይም የህዳሴ ግድብ ድርሻዎችን ለወደብ ባለቤትነት በልውውጥ ማቅረብ ለሁለቱም ወገኖች ዘላቂ ጥቅም የሚሰጥ ብልህ ዲፕሎማሲ ነው። ይህ አካሄድ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ያለውን የጥርጣሬ ድባብ በማስወገድ የቀጠናዊ ትስስር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ጥቅም ከንግድ ባለፈ ከደህንነት ጋር የተቆራኘ ነው። በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የሚታየው የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት፣ የባሕር ላይ ወንበዴነትና የሽብርተኝነት ስጋት የኢትዮጵያን ህልውና በቀጥታ ይነካል።
የራሷ የባሕር ኃይልና የወደብ ይዞታ ያላት ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም ለማስፈንና የንግድ መስመሮችን ለመጠበቅ የምታደርገው አስተዋጽኦ ለዓለም አቀፍ ንግድ ደህንነትም ትልቅ ፋይዳ አለው። ኢትዮጵያ "የመልክዓ-ምድር እስረኛ" ሆና የምትቆይበት ዘመን ማክተም አለበት። ይህ የትውልድ ጥያቄና የታሪክ አደራ ነው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከስሜታዊነት የጸዳ፣ በሕግና በፍትህ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ለቀጠናው ሰላምና ብልፅግና ዋስትና የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን የሚመጥንና ራሷ የምታስተዳድረው ወደብ ማግኘት፤ የሀገራችን ከጂኦግራፊ እስረኝነት የሚያላቅቅ ብሔራዊ ጥቅም መሆኑ ታምኖበት፣ ለተግባራዊነቱ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል። የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ብርሃንና የኢንዱስትሪ መነሳሳት እንዳረጋገጠ ሁሉ፣ የወደብ ባለቤትነት ደግሞ የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ንግድና የባሕር ላይ ክብር ዳግም እንደሚያበስር ጥርጥር የለውም። ይህ የታሪክ ጉዞ በድል እንደሚጠናቀቅ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጽኑ እምነት አለው።
በበረከት ሽመልስ
#Ethiopia #MaritimeSecurity #PortAccess #BlueEconomy #EthiopianBroadcastingCorporation