Search

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ገለልተኝነት እና ነፃነት ሕጉ እንዴት ያረጋግጣል?

ማክሰኞ ሰኔ 16, 2018 66

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተቋቋበት ዓላማ መሠረት ሥራዎቹን ሲሠራ ቆይቶ ለመጨረሻው ሀገራዊ ምክክር የመጨረሻውን ቀን ቆርጧል።

ኮሚሽኑ እያንዳንዱን ሥራውን በነጻነት እና በገለልተኝነት ነው ሲሠራ የቆየው። ለመሆኑ የኮሚሽኑን ገለልተኝነት ከሕግ አንጻር እንዴት እናረጋግጣለን?

ኮሚሽኑ የተቋቋመው በሀገራችን ያሉ መሠረታዊ የሐሳብ ልዩነቶችን በአካታች ሕዝባዊ ምክክር ለመፍታት እና ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን እና ኃላፊነቱ በተደነገገበት አዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት ኮሚሽኑ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቷል።

ይህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርገው ዋነኛው ምሰሶ የኮሚሽኑ ብቃት እና ገለልተኝነት መሆኑ በአዋጁ ላይ በግልጽ ሰፍሯል።

በአዋጁ ክፍል ሁለት አንቀጽ 4 መሠረት ኮሚሽኑ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከመንግሥት አካል ወይም ከሌላ ተጽዕኖ ነፃ ነው።

ይህ ተቋሙ ለፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን ለሀገራዊ ጥቅም ብቻ እንዲቆም የተሰጠ ትልቅ የሕግ ዋስትና ነው።

በአዋጁ አንቀጽ 6 እና አንቀጽ 3 ላይ እንደተመለከተው፣ የምክክሩ ሂደት ግልጽ በሆነ አሠራር እና በገለልተኛ አመቻችነት ይመራል።

የኮሚሽነሮቹ አሰያየም ሥርዓትም ለዚህ ማረጋገጫ ነው። በአንቀጽ 12 መሠረት ዕጩዎች በቀጥታ ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ይጠቆማሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ሰፊ ምክክር ካደረጉ በኋላ ነው የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡት። ይህም የአንድ ወገን ተጽዕኖን ያስቀራል።

በአንቀጽ 13 እና 15 መሠረት ለኮሚሽነርነት የሚመረጥ ሰው የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን የለበትም።

ኮሚሽነሩ ሁሉንም ብሔሮች እና ሃይማኖቶች በእኩል ማገልገል እና በሕዝብ ዘንድ መልካም ሥነ-ምግባር ያለው መሆን ይጠበቅበታል።

የኮሚሽኑን ገለልተኝነት እና ክብር ከሚያጎድፍ ድርጊት የመቆጠብ ግዴታም አለበት።

ሌላው የኮሚሽኑ ነፃነት ማሳያ የፋይናንስ አስተዳደሩ ነው። በአንቀጽ 27 መሠረት በጀቱ ከመንግሥት የሚመደብ ቢሆንም፣ በኮሚሽኑ ምክር ቤት በሚጸድቅ የውስጥ ደንብ መሠረት በጀቱን የማስተዳደር ሙሉ ነፃነት ተሰጥቶታል።

ይህም የዕለት ተዕለት ሥራውን ከማንኛውም የፋይናንስ ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት ይጠብቃል።

በአዋጁ የተቀመጡት የሕግ ማዕቀፎች ኮሚሽኑ ፍጹም ገለልተኛ እና ተዓማኒ ሆኖ የሀገራችንን የዘመናት ውስብስብ ችግሮች በውይይት ለመፍታት ጽኑ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።

ኮሚሽኑ በዚሁ መሰረት ሰፊውን ጊዜ ወስዶ እያንዳንዱን የማኅበረሰብ ክፍል በማካተት አጀንዳ ሲያሰባስብ ቆይቷል። አጀንዳዎቹንም በማደራጀት ሐምሌ 8 ቀን 2018 . ከሚጀመረው ማጠቃለያው የምክክር ጉባኤ አዘጋጅቷቸዋል።

በለሚ ታደሰ