የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ታሪካዊ መልዕክት አስተላልፏል።
ምርጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ እና ታሪካዊ ምዕራፍ መክፈቱን ያበሰረበት ታላቅ ክስተት ነው።
ከተመዘገበው ከ54 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ከ96 በመቶ በላይ የሚሆነው መራጭ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የምርጫው ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ነበር።
በሐረሪ ክልል 99 በመቶ፣ በድሬዳዋ 98 በመቶ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ደግሞ 97 በመቶ መራጮች ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ድምጹን ለመስጠት እስከ እኩለ ሌሊት የፀናው ይህ ሕዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።
ይህ ታሪካዊ የተሳትፎ መጠን፣ ዜጎች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በሌሎች ተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት የሚያረጋግጥ አንድ ወሳኝ እርምጃ ነው።
በሌላ በኩል ዜጎች የሀገራቸውን መጻኢ ዕድል ለመወሰን ያላቸውን ቀጥተኛ ፍላጎት እና የባለቤትነት ስሜት በጉልህ ያሳየ መሆኑን የምርጫው ውጤት አመላክቷል።
ይህ ግዙፍ የሕዝብ ተሳትፎ እና የተሰጠው ውሳኔ ያስተላለፈው መሠረታዊ የፖለቲካ መልዕክት ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር የሥልጣን መገኛ የሕዝብ ሉዓላዊ ድምጽ ብቻ መሆኑን ነው።

ሕዝቡ ረጅም ሰዓታት በትዕግሥት ተሰልፎ የጣለው እያንዳንዱ የምርጫ ካርድ በአቋራጭ የሚመጣ ሥልጣን እንደማይኖር ያረጋገጠ ነው።
ሕዝቡ ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር በጠመንጃ አፈሙዝ፣ በሁከት እና በኃይል ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚደረጉ ማናቸውንም የትጥቅ እንቅስቃሴዎች እና የኃይል አማራጮችንም ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል።
ሕዝቡ በምርጫው ያሳየው እምነት እና ቁርጠኝነት እውነተኛ እና ዘላቂ ሀገራዊ ሽግግር ሊመጣ የሚችለው የሕዝብ ውክልና በሌላቸው የፖለቲካ ልሂቃን የ"ሽግግር መንግሥት" ጥሪ ሳይሆን በሕዝብ ቀጥተኛ ይሁንታ እና በምርጫ ሳጥን ብቻ መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ ያስመሰከረበት ነው።

በመሆኑም ይህ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ የሕጋዊነት እና የተጠያቂነት መሠረትን የጣለ ነው።
ምርጫው ፓርቲዎች ያሸነፉበት ሳይሆን ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ያሸነፉበት ታሪካዊ ሁነት ሆኖ አልፏል።
ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የሰጡት ድምጽ፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና አንድነት ለማጽናት እንዲሁም ሰላም እና ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ብቸኛው እና አስተማማኙ መንገድ ምርጫ መሆኑን አስረግጧል።
ይህ ማናቸውም ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ከድምጽ ሳጥን ውስጥ ብቻ መሆኑን ሕዝቡ ያሰመረበት ታላቅ ሀገራዊ ውሳኔ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል።
በለሚ ታደሰ