Search

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጎርፍ መከላከል እና የአደጋ ዝግጁነት ሥራን በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ በይፋ አስጀመረ

ማክሰኞ ሰኔ 16, 2018 55

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጪውን የክረምት ወቅት ታሳቢ ያደረገ የጎርፍ መከላከል እና የአደጋ ቅድመ ዝግጁነት ሥራን በተደጋጋሚ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነው በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ በይፋ ማስጀመሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አቃቂ ቃሊቲ በተፈጥሯዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ የመዲናዋ ታችኛው ክፍል በመሆኑ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ተጠቂ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ለዚህ አካባቢ ቅድሚያ በመስጠት እና በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች ወንዞች ተፈጥሯዊ ፍሰታቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ የሚያስችሉ የተለያዩ ግንባታዎችን የማከናወን እና የፍሳሽ መስመሮችን የማጽዳት ሰፊ ንቅናቄ ተጀምሯል ብለዋል።

"ክረምቱን ቀድመን መዘጋጀት ያስፈልጋል" ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ መላው የከተማዋ ነዋሪ አስተዳደሩ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል እያከናወነ ባለው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ላይ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በማጽዳት እንዲሁም ደረቅ ቆሻሻን ወደ ፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎችና ቦዮች ውስጥ ባለመጣል እና በአግባቡ በማስወገድ አካባቢውን ከጎርፍ አደጋ እንዲጠብቅ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል።