Search

ከእፍታ ወደ ጥልቀት፦ የሚዲያ እመርታ ለሀገራዊ ትርክት ግንባታ

ዓርብ ሚያዝያ 30, 2018 51

በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታዩት ለውጦች ተቋማዊ ቅርፅን ከማሻሻል ባለፈ፣ የሐሳብ ነፃነትንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ፣ የሚዲያውን ጉዞ ካለፈበት የታሪክ ጠባሳ አንስቶ እስከ ነገው የዲጂታል ሉዓላዊነት ድረስ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሪፎርሙን የመጀመሪያ እርምጃ ሲያስታውሱ፣ በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን መፍታት፣ የታገዱ ሚዲያዎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ማድረግና የሳተላይት ስርጭት ዕገዳዎችን (ጃሚንግ) ማንሳት ዋነኞቹ ነበሩ።

ይህንን የነፃነት አየር ተከትሎ የመጣውን የሚዲያውን ሁኔታ "ታስሮ እንደቆየ ጥጃ" በማለት በምሳሌ አስረድተዋል። ጥጃው ሲፈታ እግሮቹ እንደፈለገ እንደማይታዘዙለት ሁሉ፣ ሚዲያችንም በሙያዊ ብቃትና በሥነ-ምግባር  ረገድ የታዩበት ክፍተቶች ነፃነትን በቅጡ ካለማስተዳደር የመነጩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ የሚስተዋሉ ግጭቶች መነሻቸው ኢትዮጵያ የተሠራችበት "አፈር" ወይም መሠረት ሳይሆን፣ የተሠራው "ጀበናና ሲኒ" ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

"የጥቁር ሕዝቦች መነሻና መገኛ መሆናችን ብዙ የሚያከራክር አይደለም፤ ፀቡ ያለው ቅርፅ ከወጣለት በኋላ ነው" ያሉት / ዐቢይ፣ የሚዲያ ተቋማት ልዩነትን ከማጉላት ይልቅ የቆየውን የጋራ ታሪክና ማንነት ወደ ማጠናከር እንዲዞሩ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም እንደ አማራና ኦሮሞ ያሉ ሕዝቦች የዘመናት የታሪክና የባህል ትስስር በሚዲያዎች ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የውጭ ሚዲያዎች "ሙቀት" እና የውስጥ ሚዲያዎች "ብርሃን"

የውጭ ሚዲያዎች ትኩረት አነጋጋሪ በሆኑ ርዕሰ ዜናዎች ላይ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ሚዲያዎች "ሙቀት" እንጂ "ብርሃን" እንደማይሰጡ አስገንዝበዋል።

የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ግን ከርዕሰ ዜና ፍጆታ ባለፈ ጉዳዮችን ከመነሻቸው የሚያዩና ለሕዝብ ብርሃን የሚሰጡ ሊሆኑ ይገባል። "የኛን መመካከርና መማማር የማይፈልጉ የውጭ አካላት የከፋውን ነገር ይፈልጋሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚዲያ ሰዎች በሐላፊነት ስሜት ብሔራዊ ጥቅምን እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል።

ቴክኖሎጂ የሚዲያውን አሠራር በከፍተኛ ፍጥነት እየቀየረው ይገኛል። እያንዳንዱ ከሚዲያ ባለሙያዎች አፍ የሚወጣ ቃል "ዳታ" መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህ መረጃ በሀገር ውስጥ እንዲቀመጥ "ናሽናል ክላውድ" የመገንባት ሥራ መጀመሩን አብስረዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ዕውቀት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘመን እንዳይበረዝ ለማድረግና የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ ነው።

አራቱ "ፒ" (4 Ps)፦ የሚዲያ ባለሙያዎች መመሪያ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማንኛውም የሚዲያ ባለሙያና ጸሐፊ አራት መሠረታዊ መመሪያዎችን አስቀምጠዋል፦

·       ፐርፐዝ (Purpose): ዜናው ወይም ጽሑፉ ለምን ዓላማ እንደሚሠራ አስቀድሞ መለየት።

·       ፐርስፔክቲቭ (Perspective): አንድን ጉዳይ ከተሟላና ከሚዛናዊ እይታ አንጻር መመልከት።

·       ፕሮፌሽናሊዝም (Professionalism): የሙያ ሥነ-ምግባርንና ሕግን አክብሮ መሥራት።

·       ፕሮክሲሚቲ (Proximity): ስለሚዘገብበት አካባቢና ማኅበረሰብ ቀርቦ ማወቅ።

"በየለም የተሞላ እሳቤ ውጤት አያመጣም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የሚዲያ ተቋማት ካሉባቸው ውስንነቶች ወጥተው ወደ መፍትሔ ማምራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ውሸትና ሴራ ለተወሰነ ጊዜ ቢሠሩም፣ የሚዘልቅና ተፅዕኖ የሚፈጥር ሚዲያ ግን በእውነትና በጥናት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ፣ ቴክኖሎጂን የታጠቀና የሀገርን መንፈስ የማይሰብር ሚዲያ መገንባት የነገዋን ብልፅግና ኢትዮጵያ ለማረጋገጥ ዋነኛው መሣሪያ ነው።